
AMN – ታኅሣሥ 01/2017 ዓ.ም
የሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በደረጃ 4 እና በደረጃ 5 በተለያዩ የቴክኒክና የሙያ ዘርፎች ለወራት ያሠለጠናቸውን ወታደራዊ ሙያተኞች፣ ሲቪል የቴክኒክ ሙያተኞች እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ሠልጣኞችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ ሥልጠና ዋና መምረያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፣ ሠራዊቱ በአደረጃጀት በትጥቅ እና በሰው ኃይል በማጎልበት ኢትዮጵያን የሚመጥን ሆኖ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
“ሠራዊታችን ጠላቱን ተዋግቶ የሚያሸንፍ ብቻም ሳይሆን ጠላቶቻችን በሩቅ የሚፈሩት እና ደጋግመው እንዲያስቡ የሚያስገድድ ሆኖባቸዋል” ያሉት ጄኔራል መኮንኑ፣ “የሀገራችንን እና የተቋማችንን ውጤታማ የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚፈታተኑ ኃይሎችን ሴራ በተሟላ ወታደራዊ ዝግጁነት እያከሸፈ ይገኛልም” ሲሉ ገልጸዋል።
የሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አበበ ዋቅሹማ በበኩላቸው፣ ኮሌጁ መከላከያ ሠራዊቱ በሚያካሂደው የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ሂደት የታጠቃቸውን የውጊያ ቴክኖሎጂዎች መንከባከብ እና መጠገን የሚችሉ የተሻለ እውቀት እና ክህሎት ያላቸውን የቴክኒክ ወታደራዊ ሙያተኞች እያፈራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ተመራቂዎች የሠራዊታችን ሁለንተናዊ የውጊያ አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ የሚሰጣቸውን ግዳጅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በብቃት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።