AMN – ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
አሸናፊውን በቀላሉ ለመገመት አደጋች የሆነው የ2024 የአሜሪክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ወደ መከፈቱ ናቸው።
ከ78 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ግን መደበኛው የምርጫ ሥነ-ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት አስቀድመው ድምፃቸውን መስጠታቸው ተመላክቷል።
አሁን ባለው የምርጫ ቅድመ ግምት ትንተናዎች ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሐሪስ አንገት ለአንገት ተናንቀዋል።
ካማላ ሐሪስ ጽኑ የዴሞክራት ደጋፊ ግዛቶች 226 ኤሌክቶራል ኮሌጅ አስተማማኝ መነሻ ድምፅ ያላቸው ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ጽኑ የሪፓብሊካን ደጋፊ ከሆኑ ግዛቶች 219 ኤሌክቶራል ኮሌጅ አስተማማኝ መነሻ ድምፅ እንዳላቸው ተነግሯል።
ከዚህም የተነሣ ዋዣቂ ግዛቶች ላይ በሚደረገው ፈልሚያ የምርጫው ሙጤት የሚወሰን ይሆናል።
በአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት መሠረት አንድ እጩ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመመረጥ ካሉት 538 ኤሌክቶራል ኮሌጅ 270 እና ከዚያ በላይ ማሸነፍ የግድ ይለዋል።
ፔንሲልቫኒያ የዘንድሮውን የአሜሪካ ምርጫ አሸነፊ የምትወስን ግዛት ትመስላለች።
ከሁሉም ግዛቶች ይልቅ በእጩዎቹ በተደጋጋሚ የተጎበኘችው የፔንሲልቫኒያ ግዛት ስትሆን፣ ሁለቱም እጩዎች የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻቸው ያደረጉት በዚሁ ግዛት ነው።
ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ ያልለየላቸው ዋዣቂ ግዛቶች መካክል ከፍተኛው ኤሌክቶራል ኮሌጅ የምትይዘው ፔንሲልቫኒያ ግዛት 19 ኤሌክቶራል ኮሌጅ አላት።
የዚህች ግዛት ሕዝብ ድምፅ ማግኘት ወደ 270 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ለመቅረብ ወሳኝ ነው።
የቢቢሲ እና የአሜሪካ ድምፅ ዘገባ እንዳመላከተው፣ በ2020 የአሜሪካ ምርጫ የዴሞክራቱ እጩ ጆ ባይደን በዚህ ግዛት ያሸነፉ ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ ፔንሲልቫኒያ ላይ ዶናልድ ትራምፕ በከማላ ሐሪስ ዳግም የሚሸነፉ ከሆነ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት የመግባት ዕድላቸው የጠበበ ይሆናል።
በአሳየኛቸው ክፍሌ