AMN- ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም
የምስራቅ ቦረና ዝናብ አጠር አካባቢ ፣ የአርብቶ አደሮችን ሕይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሸመልስ አብዲሳ ገልፀዋል ።
የአርብቶ አደር አካባቢን ወደ ተሻለ ሕይወት መቀየር ከተቻለ አገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሸመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
በዛሬው ዕለት በምስራቅ ቦረና ዞን በሊበን ወረዳ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሰንዴ ምርት በኮምባይነር የማጨድና የመውቃት ስራን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሸመልስ አብዲሳ አስጀምረዋል።
በመርሀግብሩ በዞኑ ውሃ ማስተዳደር ፣ ትናንሽ እና መካከለኛ ግድቦች ጨምሮ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ስራዎች ከማህበረሰቡ ጋር በትብብር በመሰራቱ በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ዞኑ የጸጥታ ችግር የነበረበት አካባቢ መሆኑን አስታውሰው ፣ መንግስት እና ሕዝብ በጋራ ተቀናጅተው በመስራታቸው ለዛሬ ቀን በቅቷል ብለዋል።
ይህ በቦረና ዞን የተገኘው ስኬት የአርብቶ አደር አካባቢዎች ሕይወት ከመቀየር ባለፈው ለኢትዮጵያ አልፎም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚተርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ ከ71 ሺህ ሄክታር በላይ የስንዴ ምርት በኮምባይነር የማጨድና የመውቃት ስራ እየተከናወነ ሲሆን ፣ በሊበን ወረዳ በዛሬው ዕለት ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሰንዴ ምርት በኮምባይነር የማጨድና የመውቃት ስራ ተጀምሯል።
በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ እንደታቀደ የዞኑ የግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በዞኑ በአጠቃላይ ከ1 መቶ 43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ምርቶች በክላስተር መሸፈኑም ተገልጿል።
በዳንኤል መላኩ