AMN – ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም
የምስራቅ ቦረና ዞን አርብቶ አደሮች ከመኸር አዝመራ የሰብል ልማት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው አርብቶ አደሮች ተናገሩ።
በዞኑ በ5 ዋና ዋና ሰብሎች ከለማ መሬት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የመኸር አዝመራ ዘግይቶ ከሚለማባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አንዱ ምስራቅ ቦረና ዞን ሲሆን የመኸር ወቅቱም ከመስከረም እስከ ህዳር አጋማሽ ይዘልቃል።
በዞኑ ሊበን ወረዳ የሲሚንቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሀሮ ዋቆ እንዳሉት በአካባቢያቸው በየአመቱ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ዝናብ ቢጥልም በልምድ ማነስ ከእንስሳት ግጦሽ ያለፈ ለሰብል ልማት ሳይጠቀሙበት ያልፋል፡፡
ከሶስት ዓመታት ወዲህ ግን በግብርና ባለሙያዎች ምክርና ግፊት ፈጥነው የሚደርሱ የተለያዩ ሰብሎችን ማልማት እንደጀመሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፈው አመት በመኸር ወቅት ካለሙት ሁለት ሄክታር መሬት 25 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰው ዘንድሮም ካለፈው አመት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ በማቀድ ሶስት ሄክታር መሬት በቦለቄ፣ ጤፍና ስንዴ ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲ ኑር፣ ዘንድሮ በሰብል ልማቱ ከተሳተፉ አርብቶ አደሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ ሁለት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም ከሁለት ሄክታር መሬት አብዛኛውን በጤፍ ቀሪውን ቦለቄ ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለልማቱ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ከሄክታር እስከ 35 ኩንታል አጠቃላይ ምርት ለማግኘት የሰብል እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሊበን ቦሩ፣ ዘንድሮ 130 ሺህ ሄክታር መሬት በመኸር አዝመራ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች እስካሁን 115 ሺህ ሄክታር መሬት ጤፍ፣ ቦለቄ፣ የስንዴ፣ ሽንብራ እና ሰሊጥን ጨምሮ ፈጥነው በሚደርሱ ሰብሎች እየለማ መሆኑን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡።
የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግም 18 ሺህ 960 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉንም አስታውቀዋል፡፡
በሰብል ልማቱም 98 ሺህ 77 አርብቶ አደሮች እና አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሆነ አክለዋል።