የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት በቀጣናዉ ያለዉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በተገቢዉ መንገድ ለመጠቀም በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ፡-ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

You are currently viewing የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት በቀጣናዉ ያለዉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በተገቢዉ መንገድ ለመጠቀም በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ፡-ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

AMN- መስከረም 9/2017 ዓ.ም

የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት በቀጣናዉ ያለዉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በተገቢዉ መንገድ ለመጠቀም በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አሳሰቡ ።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዘም ሃብት ለመጠቀም ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነዉ ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ናቸዉ ።

የምስራቅ አፍረካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት /ኢጋድ/ የ 10 አመት ዘላቂ የቱሪዝም ልማት መሪ እቅዱን በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ ይፋ አድርጓል ።

ከፈረንጆቹ 2024 _ 2034 የሚዘልቀዉ የድርጅቱ የቱሪዝም መሪ እቅድ አባል ሃገራቱ በቀጠናዉ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የጋራ እና የተቀናጀ በማድረግ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ አላማዉን ያደረገ ነዉ ።

አባል ሃገራቱ በዘርፉ እምቅ አቅም ያላቸዉ እና በተፈጥሮ ለቱሪዘም የተመቹ ቢሆኑም በተለያዩ ሰዉ ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ያላቸዉን አቅም መጠቀም አለመቻላቸዉ ይነገራል ።

ግልጽ የሆነ ሀገራዊ ፖሊሲ ያለመኖር ፣ ወጥ የሆኑ መመሪያዎች ያለመኖር ፣የመረጃ እጥረት ፣የተገደበ የቪዛ ስርአት ፣ የአየር ንብረት ለዉጥ ተጋላጭነት ፣ ግጭት እና የመሳሰሉት በቀጠናዉ የቱሪዝም ዘርፉ ይሄ ነዉ የሚባል እድገት እንዳያስመዘግብ ማነቆ ከሆኑት ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል ።

የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሌ፣ የድርጅቱ የቱሪዝም ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ እንግዶች በተገኙበት ኢጋድ የአስር አመቱን ዘላቂ የቱሪዘም መሪ እቅዱን ይፋ ያደረገዉ ።

ዋና ጸሃፊዉ ወርቅነህ ገበየሁ ባስተላለፉት መልእክት እቅዱ በሀገራቱ መካከል ያለዉን አንድነትና ትብብር በማጠናከር ተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ የቱሪዘም ልማትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል ።

ከዚህ ባሻገርም በሃገራቱ መካከል ያለዉን ወንድማማችነት ለማጠናከር የሚረዳ ልዩ አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል ። ሀገራቱ ይህንን መልካም አጋጣሚ ባግባቡ እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ እና ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል ።

አለማቀፍ ደረጃቸዉን የጠበቁ የቱሪዘም መዳረሻዎችንም በስፋት በማልማት ላይ መገኘቷን አንስተዋል ።

የቱሪዘም ዘርፉን ከአምስቱ የልማት እቅድ መሰሶዎች ዉስጥ አንዱ አድርጋ በፖሊሲ አካታ መያዟንም አስምረዉበታል ።

ዛሬ ይፋ የተደረገዉም የኢጋድ ዘላቂ የቱሪዝም መሪ እቀድም ዘርፉን ለማሳደግ በተበታተነ መልኩ የሚደረገዉን ጥረት ወደ አንድ የሚያመጣ በመሆኑ ለእቅዱ ስኬት ኢትዮጵያ ጥረት ታደርጋለችም ብለዋል ።

በአለማየሁ አዲሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review