የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት ከኬንያ ወደ ታንዛንያ የሚያስተላልፈው መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት ጀመረ

AMN-ታህሣሥ 6/2017 ዓ.ም

የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ (East Africa Electric Highway) ፕሮጀክት የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የታንዛንያ የሀይል መሰረተልማት አካል የሆነው ኃይል ከኬንያ ወደ ታንዛንያ የሚያስተላልፈው መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት መጀመሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት የመጀመሪያው የኃይል ትስስር በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል የተፈጠረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በተዘረጋው የኃይል አቅርቦት መሰረተልማት በኩል የኃይል ትስስሩ እውን ሆኗል ነው የተባለው፡፡

የፕሮጀክቱ ሁለተኛና ከኢትዮጵያ – ኬንያ ፕሮጀክት በመቀጠል በኬኒያና በታንዛንያ መካካል የተዘረጋው የኃይል አቅርቦት ትስስር መስመር መሆኑ ተመላክቷል።

ይህ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠናቆ የሙከራ ኃይል አቅርቦት መጀመሩን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ ቀጠናዊ የኃይል ትስስር በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማረጋገጥ በሀገራት መካካል ትብብርን በማምጣት ብልጽግናን ያሰፍናል ተብሏል፡፡

የኃይል ትስስሩ ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በማስፋፋት የአረንጓዴ የኤሌክትሪክ ኃይል ግብይትን በቀጠናው እንዲስፋፋ ሚና እንድትጫወት በማስቻል በመጀመሪያዎቹ የግብይት ዘመናት በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ እንድታገኝም እንደሚያደርጋት ተገልጿል።

ለፕሮጀክቱ የአለም ባንክ ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የፈረንሳይ የልማት ፋይናንስ ተቋም ድጋፍ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review