
AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም
በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የግዳጅ ቀጠና ላይ የተሰማራው የምዕራብ ዕዝ ኮር በተደጋጋሚ ባከናወነው ጠንካራ እርምጃ ፅንፈኛውን ቆሞ እንዳይዋጋ ማድረጉን አስታውቋል።
ፅንፈኛ ቡድኑ በተበተነባቸው የእነብሴ ሳር ምድር፣ ዲጎ ፂዮን፣ ስናን፣ ባሶ ሊበንና ሸበል በረንታ አካባቢዎች እስከ አባይ በርሀ አዋሳኝ ቦታዎች አሰሳ በማድረግ የቡድኑን ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ አቅም ማሳጣት ተችሏል ሲሉ የኮሩ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አዘዘው መኮነን ተናግረዋል።
ፅንፈኛው የመሸገባቸውን ቦታዎች በመቆጣጠር እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ በዋናነት ይልቃል አለሙ፣ ይበልጣል በየነ፣ ሰውአለ አንማው፣ ጌትዬ ሳለው፣ በለጠ ልየውና ድረስ አንድአርግ የሚባሉ የቡዱኑ መሪዎች እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።
የኮሩ አንድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ገብረህይወት ሠራዊቱ ባደረገው ኦፕሬሽን ፅንፈኛው ላይ በተወሰደ እርምጃ 99 ታጣቂዎች በመደምሰስ ፣ 82 በማቁሰል፣ 8 በመማረክ ክላሽ፣ ብሬን፣ ቦምብ ፣ ካዝና፣ ትጥቅ፣ ሞተር ሳይክል ፣ የመገናኛ ራዲዮን ከመንግስትና ከግል መስሪያ ቤት የተዘረፉ የቢሮ እቃዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማኀበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።