የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሃገራዊ አጀንዳን ሁሉም የጋራ ሊያደርገው ይገባል ፡- ቢቂላ ሁሪሳ ( ዶ/ር )

You are currently viewing የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሃገራዊ አጀንዳን ሁሉም የጋራ ሊያደርገው ይገባል ፡- ቢቂላ ሁሪሳ ( ዶ/ር )

AMN- ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ታላቅ ሚና ባለዉ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሃገራዊ አጀንዳን ሁሉም የጋራ እንዲያደርገዉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማእከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ ( ዶ/ር ) ጠየቁ ።

ሉዓላዊነት በምርታማነት በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።

መድረኩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በጋራ በመሆን ያሰናዱት ነዉ ።

በመድረኩ ላይ ሚኒስትሩ ቢቂላ ሁሬሳ ( ዶ/ር ) ሀገራዊ ሉአላዊነትን ማስከበር የኢትዮጵያ ቁልፍ አጀንዳ ከሆነ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህ ቁልፍ አጀንዳ ዉስጥ ደግሞ ራስን በምግብ መቻል ዋናዉ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ባለፉት አመታት ተሰርቶበታልም ነዉ ያሉት ።

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ያደረገችዉ እንቅስቃሴ ታላቅ ዉጤት የተገኘበት መሆኑንም ጠቁመዋል ።

የሌማት ትሩፋትን በማሳደግ ከነብስ ወከፍ ገቢ ጨምሮ በሀገር ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል ።

እየመጣ ያለዉ ተጨባጭ ዉጤትም ኢትዮጵያ በዘርፉ ታላቅ አቅም እንዳላት ያረጋገጠም ነዉ ብለዋል ።

በዉጤቱም ከዉጭ ይገቡ የነበሩ የግብርና ምርት አይነቶችን በሀገር ዉስጥ በስፋት ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል ።

በተለይ የስንዴ ምርትን በሀገር ዉስጥ በማምረት ወደ ዉጭ ሀገር መላክ መቻሉ ኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የሄደችበት ርቀት እና ዉጤቱን ያረጋገጠ ነዉም ብለዋል ።

ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ታላቂ ሚና ባለዉ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሃገራዊ አጀንዳን ሁሉም የጋራ እንዲያደርገዉም ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸዉ አለማቀፋዊ ድጋፍ ላይ መንጠልጠል ሉአላዊነትን ተጋፍቶ ጥገኝነትን የሚያጎላ መሆኑን አስታውሰዋል ።

ሉአላዊነትን ለማረጋገጥም ሀገራዊ ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተኪ የሌለዉ አማራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የምግብ ሉዓላዊነት ከአገር ሉዓላዊነት ጋር ያለው ትስስር ምን ያክል ነዉ ፣ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ቅነሳ ፖሊሲ አኳያ ያለው መስተጋብር እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና በሚሉ ሃሳቦች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸዉ ነዉ ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያሉ ምቹ ሁኔታዎች ምንድናቸዉ የሚለዉም በውይይቱ በስፋት እየተዳሰሱ ካሉት አንኳር ጉዳዮች መካከል ነዉ።

በፓናል ውይይቱ ሚኒስትሮች ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ ምሁራን፣ የኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙሀን ሃላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል ።

አለማየሁ አዲሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review