AMN – የካቲት 13/2017 ዓ.ም
የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር ሚስዝ ቫለቲና ማትቬንኮ ለሁለት ቀናት ያካሄዱትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ወደአገራቸው ሲመለሱ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማሪፊያ በመገኘት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡
ሚስዝ ቫለቲና ማትቬንኮ በተደረገላቸው ድንቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸውን በእሳቸውና በልዑካን ቡድናቸው ስም አቅርበው በሁለቱ ቀናት ባካሄዱት የሥራ ጉብኝት በእጅጉ መደሰታቸውን እና የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጠንካራና የማይናጋ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መመልከታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ ሚስዝ ቫለቲና ማትቬንኮ እና የልዑካን ቡድኑ ባለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ በመገኘት ባካሄደው የሥራ ጉብኝት እና ውይይት በእጅጉ መርካታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሩሲያ እና ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት ጸንቶ የቆየው መልካም ዲፕሎማሲያዊ አጋርነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት በመግለጽ እንዳሰናበቷቸው የፌደሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያሳያል፡፡