ራስ ምታት በጭንቅላት ወይም በፊት ላይ የሚሰማ ህመም ነው፡፡
ራስ ምታት ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው የሚያጋጥማቸው የተለመደ በሽታ ሲሆን፤ እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከ150 በላይ የራስ ምታት ህመም አይነቶች አሉ፡፡
ይህ በሽታ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚይዝ ሲሆን፤ በአንጎል፣ በደም ስሮች እና በአቅራቢያቸው ባሉ ነርቮች አማካኝነት የሚመጣ ድብልቅ ህመም እንደሆነም ነው መረጃቹ የሚጠቁሙት፡፡
ራስ ምታት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ በመባል በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ይከፈላል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ራስ ምታት የሚባለው ብዙ ጊዜ የሚያጋጥምና የተዘወተረ ሲሆን፤ ለከፋ ጉዳት የማይሰጥ እንደሆነ ነው የጤና መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
ለአብነትም፡-በጭንቀት ምክንያት የሚከሰት ራስ ምታት፣ ማይግሬን እና ቅጽበታዊ ራስ ምታት ህመሞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አንዳንድ የመጀመሪያ ደረጃ ራስ ምታት አይነቶች በአኗኗር ሁኔታዎች ወይም በአመጋገብ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ለምሳሌ በአልኮሆል መጠጦች፣ በምግብ፣ በእንቅልፍ መዛባት ወይም ማጣት፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ በረሃብ፣ በማሳል፣ በማስነጠስ፣ በከፍተኛ ሁኔታ በመሳቅ ወይም በማልቀስ እና በመሳሰሉት ይከሰታሉ፡፡
እነዚህ የራስ ምታት አይነቶች በአብዛኛው ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉ ባይሆኑም ሰዎችን የሚያሠቃዩ እና በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ መሆናቸውን የጤና መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የራስ ምታት የሚባለው ደግሞ ሥር የሰደደ የጤና እክል የሚያስከትልና እንደ የበሽታ ምልክት ሆኖ ሊቆጠር የሚችል መሆኑን ነው የጤና መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
አብዛኛዎቹ የሁለተኛ ደረጃ የራስ ምታት አይነቶች ለሌላ ከባድ በሽታ ምልክት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቀሳል፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የራስ ምታት ከሚባሉት ውስጥ ከአከርካሪ አጥንት ፈሳሽ ጋር የሚገናኝ ራስ ምታት፣ በድንገት የሚመጣ እጅግ በጣም የሚያሠቃይ ራስ ምታትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ምልክቶች አንዳንዴ ለከባድ ወይም ለሕይወት አስጊ ለሆኑ እንደ የጭንቅላት ጉዳት፣ የአዕምሮ ደም መፍሰስ፣ የከፍተኛ ደም ግፊት መጨመር ምልክት ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ራስ ምታት ከነርቭ ሕመም ምልክቶች ጋር የሚቆራኝ ከሆነ ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ነው የጤና መረጃዎች የሚጠቁመት፡፡
ለምሳሌ፡- ድካም፣ መፍዘዝ፣ በድንገት ሚዛንን ማጣት ወይም መውደቅ፣ የመደንዘዝ ስሜት መሰማት፣ መንቀሳቀስ ያለመቻልና ሽባ መሆን፣ የንግግር ችግር፣ ግራ መጋባት፣ የስብዕና ለውጦች (ተገቢ ያልሆነ ባህርይ ማሳየት)፣ የእይታ መደብዘዝ ወዘተ ሲያጋጥሙ ቶሎ ብሎ ወደ ህክምና መሄድ ተገቢነት እንዳለው ይመከራል፡፡
መከላከያ መንገድ
በዓለማችን በርካታ የራስ ምታት ያለባቸው ሰዎች ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው እንደማይመረመሩና ተገቢውን ህክምና እንደማያገኙ የዓለም ጤና ድርጅት ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ይፍ አድርጓል፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሽታውን አቃሎ የማየትና የግንዘቤ እጥረት አንዱ ሲሆን፤ በዘርፉ ያሉ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎችም የእውቀት ማነስ ዋነኛው እንቅፋት ነው ይላል የዓለም የጤና ድርጅት፡፡
ሆኖም የራስ ምታት ሕመምን ለመከላከል ቀላል የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል፣ በመስኩ በሰለጠነ ባለሙያ ትክክለኛ ምርመራ ማድረግ እና የራስ ምታት በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ በባለ ሙያ የታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ ተገቢ እንደሆነም የዓለም የጤና ድርጅት ይመክራል፡፡