የሰላምና ጸጥታ አገልግሎት ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ዋስትናና መሰረት በመሆኑ ትልቅ ክብር እንሰጣለን ፡-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የሰላምና ጸጥታ አገልግሎት ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ዋስትናና መሰረት በመሆኑ ትልቅ ክብር እንሰጣለን ፡-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

የሰላምና ጸጥታ አገልግሎት ለሁለንተናዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስኬት እንዲሁም ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ዋስትናና መሰረት በመሆኑ ትልቅ ክብር እንሰጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ መምሪያዎች፣ አመራሮች፣ አባላት እና አጋር አካላት እውቅና ሰጥቷል።

የሰላምና ጸጥታ አገልግሎት ውጭ ውሎ ከማደር እስከ አካል መጉደል እና የህይወት መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት ከንቲባ አዴነች አቤቤ ይህ በከፍተኛ መሠጠት የሚከናወን ተግባር በመሆኑ ክብር መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

አዲስ አበባን የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ታቅዶ በርካታ ፈተናዎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሲያጋጥሙ ቢቆዩም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላትና ከህዝቡም ጋር በመቀናጀት በጀግንነት ፈተናዎቹን ማለፍ ችሏል ያሉት ከንቲባ አዳነች በዚህም ውስጥ በርካታ ትምህርቶች ፣ የወንጀል መከላከል ስልቶችና ታክቲኮች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስን የወንጀል መከላከል እና የተደራሽነት አቅም ለማሳደግ የሰው ሀይል ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን፣ የፖሊስ ጣቢያዎች ብዛት በእጥፍ ማደጋቸውን ፣ የፖሊስ መምሪያዎች የየራሳቸው ዘመናዊ የማዘዣ ጣቢያ ህንጻዎች እንዲኖራቸው መደረጉን፣ ዘመኑን የዋጀ የፖሊስ አገልግሎት እንዲኖር በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን እንዲሁም በየግዜው የፖሊስ አመራሮችን እና አባላትን አቅም ለመገንባት ተከታታይ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸው ገልጸዋል።

ይህም የከተማዋ ፖሊስ በሁለንተናዊ መልኩ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ እንዳስቻለው ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሪፎርም በኋላ በስራ አፈጻጸም፣ በሰው ሀይል ብቃት ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በአጠቃላይ ፖሊሳዊ ተልዕኮ አፈጻጸም ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ የተሻለ የጸጥታ ስራ ቢሰራባትም የተለያዩ የሽብር ስጋቶችም አሉባት ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ለዚህ የሚመጥን የጸጥታ ስራም እየተሰራባት ነው ብለዋል።

የከተማዋ የጸጥታ አጠባበቅ ለሌሎች አደጉ ለሚባሉ ከተሞች ሁሉ ተምሳሌት የሆነ ነውም ብለዋል።

በከተማዋ የሽብር ሀይሎች በቀላሉ ዘልቀው የማይገቡበት ጠንካራ የጸጥታ እና ህዝብን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አዛዡ ከተማዋ ወደ ስማርት ከተማነት እያደገች በመምጣቷ ይህንን የሚመጥን ስማርት የፖሊስ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት የተሻለ የመኖሪያ ቤት እና ካምፕ እንዲኖራቸው በቀጣይ እንደሚሰራም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋ አድርገዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review