የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ ታጣቂዎችን አርአያነት በመከተል የቀሩትም እንዲመጡ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጥሪ አቀረበ

You are currently viewing የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ ታጣቂዎችን አርአያነት በመከተል የቀሩትም እንዲመጡ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጥሪ አቀረበ

AMN – ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር አባላት መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት የተመለሱ ታጣቂዎችን አርአያነት በመከተል የቀሩትም እንዲመጡ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ጥሪ አቀረበ።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል የድርሻውን እንደሚወጣም ህብረቱ አስታውቋል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ ዛሬ በአዳማ ከተማ መግለጫ ተሰጥቷል።

የህብረቱ ሰብሳቢና የመጫ ኦሮሞ አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በመግለጫቸው፤ በጫካ የቀሩ ታጣቂዎች የቀረበውን “የሰላም አማራጭ በመከተል እንዲገቡ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጫካ ያሉ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ሰምተው እንዲመለሱ ዳግም ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።

ሃዳ ሲንቄዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን ጨምሮ ሌሎችም ሰላምን በመስበክ “በክልሉ የተገኘውን ሰላምና ዕርቅ ለማፅናት ተባብረን መስራት ይገባናል” ብለዋል።

“የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች በማህበራዊ የትስስር ገፆች የሚናፈሱ አሉባልታዎችና መሰረት ቢስ ወሬዎችን በመተው ለሰላምና ለአንድነት ዘብ መቆም አለብን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህብረቱ አባልና የሲኮ መንዶ አባ ገዳ አሊይ ሙሐመድ ሱሩር በበኩላቸው፤የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች በክልሉ ዕርቅና ተስፋ እንዲለመልም ያስችላሉ ጀግኖችም ናቸው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ውጭ እየኖሩ በአሉባልታና የሐሰት መረጃ በማሰራጨት ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በክልሉ የነበረው ችግር ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርስ እንደቆየ በማስታወስ ሁሉም የተዘረጋውን የሰላም አማራጭ መቀበል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የቀድሞ የቱለማ አባገዳ ሃዩ ለገሰ ነገዎ ናቸው።

ችግሩን ለመፍታት መስማማትና መግባባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመው፥ ለዚህም የሰላም አማራጭ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የተጀመረው የሰላም ስምምነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻችንን መወጣት አለብን ነው ያሉት።

ሃዳ ሲንቄ አፀዱ ቶላ በበኩላቸው፤የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የገቡ ታጣቂዎች የሰላም ጀግኖች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወጥቶ መግባት ስጋት ሆኖብን ነበር፤ “አሁን የተገኘው የሰላም ተስፋ ውጤታማ እንዲሆን ጫካ የተቀሩም እንዲመጡ ዳግም ጥሪ እናደርጋለን” ሲሉ አስታውቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review