የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር እየተደረገ ባለው ውይይት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም

የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር እየተደረገ ባለው ውይይት በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለኦሮሞ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ሲባል ልዩነትን ለማጥበብና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉ የሸኔ አመራርና አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።

በውይይቱም በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑንም መግለጫው አረጋግጧል።

ለውጡ ከመጣ ቀን ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ለተላለያየ ችግር የሚጋለጠው የውስጥ አንድነት በማጣቱ መሆኑ ታምኖበት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህዝቡ አንድነት ያልተነሳበት መድረክ እንዳልነበረ በመግለጫው ተመልክቷል።

ሲደረግ የነበረው የሰላም ጥሪም ያለማቋረጥ እንደነበረ ገልጾ የኦሮሞ ህዝብ በተለያየ ጊዜ ያደረጋቸው ትግሎች ፍሬ ያላፈሩት በውስጥ አንድነት እጦት መሆኑን መግለጫው አክሎ አትቷል።

የለውጡ መምጣትም የኦሮሞን ህዝብ አንድነት የበለጠ እንደሚያጠናክር በማመን የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተሰራው ስራ ትልቅ እድል እንደነበረ ተመልክቷል።

በወቅቱ መልካም ጅማሮዎች እንደነበሩ ቢታወቅም ብዙም ሳይቆይ በመሳሳብና አንዱ ለሌላው እንቅፋት በመሆኑ ችግሩ ለስድስት ዓመታት ዘልቋል።

ህዝቡም ያልተገባ መሰዋእትነት እንዲከፍል መገደዱን ያተተው መግለጫው የስድስት ዓመታቱ የለውጥ ጉዞ በሰላማዊ ጉዞ የታጀበ ቢሆን ሮኖ ብዙ ርቀት መጓዝ ይቻል እንደነበረም አንስቷል።

ይህ ችግር እንዲቆምና በኦሮሞ መካከል አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ እንደ መንግስትም ሆነ እንደ ብልጽግና ፓርቲ የሰላም ጥሪ ያልቀረበበት ጊዜ እንደሌለም መግለጫው ያስታውሳል።

ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር የተደረገ የሰላም ውይይት ባይሳካም ተስፋ በመቁረጥ የሰላም መንገዱ እንዳልተዘጋና ይልቁንም በተከታታይ የሰላም ጥሪ ሲቀርብ እንደነበረ መግለጫው ያመለክታል።

የኦሮሞ ሕዝብም እንደ ባህሉና እንደ ወጉ እንዲሁም በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን እነዚህ የሰላም ጥሪዎች ውጤት አላፈሩም ማለት አይቻልም ሲል መግለጫው አንስቷል።

በሺህ የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ተመልሰዋል፤ የተሃድሶ ስልጠና ወስደውም ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ለብዙዎቹም የስራ እድል ተፈጥሯል ብሏል።

ሰሞኑን በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም በርካታ ወጣቶች የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን ያብራራው መግላጫው ሰላምን ተጠምቶ የነበረው ህዝብም የክብር አቀባበል እያደረገ ይገኛል ብሏል።

አሁንም ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚቻለው ከቡድኑ አመራር አባላት ጋር ስምምነትና መግባባት ሲፈጠር በመሆኑ ከቡድኑ አመራሮች ጋር ያልተቋረጠ ውይይት ሲደረግ መቆየቱም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ውይይቱም በክልሉ ውስጥ እርቅና ሰላም ማውረድ ላይ አተኩሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን የሰላም መንገድ አዋጭ መሆኑን ከተቀበሉ አመራርና አባላት ጋር በተደረገው ውይይት መግባባት እየተፈጠረ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና ለሰላም የተከፈተው በርም ክፍት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review