በሀገራችን የሚገኙ አብዛኞቹ መዝገበ ቃላቶች ተመሳሳይ ትርጉም ሰጥተውት የሚገኝ ሲሆን
ሰንደቅ፡ ማለት “ምርኩዝ፣ ምሰሶ፣ በትር፣ ህዝብ “ማለት ነው፡፡
ዓላማ፡ “ምልክት፣ የህዝቦች የማንነት መለያ” ማለት ነው፡፡ ይህም ሰንደቅ ዓላማ “የአንድ ሀገር መንግስትና ህዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ስልጣን፣ ነፃነት፣ እድገትና ማህበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ ነው፡፡” የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ከምልክትነት ከፍ ያለ ነው፡፡ ዜጎች ከሰንደቅ ዓላማው ፊት በቆሙ ቁጥር ልዩ ስሜት ውስጥ የሚገቡት በሀገርና በህዝብ ፊት እንደቆሙ ስለሚቆጥሩ ነው፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት የህዝብና የሀገር ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት ከፍ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የህዝብ ያለፈ ታሪክ፣ ወቅታዊ ገጽታና የወደፊት ዓላማ ነፀብራቅም ነው፡፡
ለሀገርና ለህዝብ የጠለቀ ፍቅር፣ ክብርና ቁርጠኝነት ያለው ዜጋ የተግባር ልዕልና የሚገለጠውም ሰንደቅ ዓላማውን በሰቀለበት ማማ ከፍታ ነው፡፡ በተቃራኒው የሰንደቅ ዓላማ መውረድ/መረገጥ የሀገርና የህዝብ ሽንፈት ወይም ውርደት ምልክት ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገርና ህዝብ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ምልክት (መገለጫ) ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የህዝቦች ባህል፣ እምነትና መገለጫ እንዲሆን ተደገርጎ የሚቀረጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፣ የኢምባሲና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሀገሮች ውክልና የሚገለፀው በሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡
የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት መግለጫ ነው፡፡
የኢፌዲሪ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ትርጉም፡-
አረንጓዴው፡- የስራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት (አንቀፅ 7/1/)
ቢጫው፡- የተስፋ፣ የፍትሕና የእኩልነት ምልክት (አንቀፅ 7/2/)
ቀዩ ፡- ለነፃነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋእትነትና የጀግንነት ምልክት (አንቀፅ 7/3/) ነው፡፡
የኢፌዲሪ ብሔራዊ ዓርማ ትርጉም
ዓርማው ብዝሀነትን በአግባቡና በብቃት በማስተናገድ፣ የግለሰብ ነፃነቶችና መብቶችን በአግባቡ በማክበርና ለቡድን መብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገንባት ነው፡፡
አስተማማኝ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፤ የኢፌዴሪ መንግስት ከማናቸውም ሃይማኖታዊ ምልክቶች ወይም እምነቶች ጋር የማይያያዝ ወይም የማይወግን መሆኑን እና ተቻችሎና ተከባብሮ በነፃነት የመኖር ተስፋቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡
ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች፡- የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶች እኩልነትን (አንቀፅ 8/2/)፣
ቀጥታና እኩል ከሆኑ መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት፣
ቢጫ ጨረር በመፈቃቀድ አንድነት ለመሰረቱት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ይጠቁማል፡፡ (አንቀፅ 8/3/)
ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡