AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የአሜርካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ አይዲ) በማህበራዊ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሚሽን ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር በወጣቶች ስብዕና ማጎልበቻ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መደገፍ፣ ወጣቶች ላይ ትኩረት ባደረገው በዩ ሪፖርት ዙሪያ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በተመሳሳይ አመራሮቹ በሴቶች ግብርና ተጠቃሚነት፣ በሴቶች ዲጂታል ግብርና፣ በማህበራዊ ጥበቃ ኮንፈረንስ እና በሎሎች ጉዳዮች ላይም አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መልካም ግንኙንት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እያደረገች ባለው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሪፎርም ጉዳዮች ላይ ድርጅቱ እያደረገ ያለውንም ድጋፍ አድንቀዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡት ኃላፊነትና ተግባራት አንጻር እየተሰሩ ያሉትን ሥራዎች በመግለጽ በተለይ የሴቶችን እኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጁ ፕሮጅክቶችን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተራዳኦ ድርጅት ሚሽን ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር በበኩላቸው፤ የቀረበውን ሀሳብ አድንቀው በማህበራዊና ተያያዥ ጉዳዩች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።