የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል የፊልም ጥበብ አበርክቶ

You are currently viewing የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል የፊልም ጥበብ አበርክቶ

ፊልም ሰዎችን እያዝናኑ ለማስተማር፣ የሌሎችን ህይወት እና ልምድ ለማካፈል ተመራጭ የጥበብ መንገድ ነው። ማህበረሰባችን እና ባህሎቻችን እንዴት እንደሚሰሩ፣ አዲስ አስተሳሰብን እንዴት መላመድ እንዳለብን፣ ማህበራዊ ህይወታችን እና ንቃታችን ምን መምሰል እንዳለበት የእውቀት ብርሃን ለማብራት የሚረዳ ኃይለኛ ጥበባዊ መሳሪያ ነው።

ድራማዎች፣ አጫጭር ፊልሞች፣ ሲትኮም እና ተከታታይ ፊልሞች የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ወሳኝ አካል ሆነዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ፊልሞች በማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤን ያሳድጋሉ፡፡ ያስተምራሉ፡፡ ለለውጥ ያነሳሳሉ፡፡ 

በፊልሞች ላይ የሚታዩ ገጸ ባህርያት  የህይወት ውጣ ውረዶችን በማሸነፍ፣ ህልማቸውን የሚያሳኩ እና በዓለም ላይ በጎ ተጽእኖ የሚፈጥሩ፣ ሌሎችን የሚያስተምሩ፣ አንዳንዴም የሚያሳዝኑ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በማሳዘን ውስጥ ስሜትን ነክተው የሰዎችን አስተሳሰብ የሚቀይሩና ማህበረሰብን ለለውጥ የሚያነሳሱ ይሆናሉ፡፡ ፊልሞች የሴቶችን ጥቃት ለመከላከልና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡

የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በመጪው ሰኞ የሚከበረውን “በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የማስወገድ ዓለም አቀፍ ቀን” መነሻ በማድረግ የሴቶች ጥቃትን በተመለከተ የተሰሩና ለጉዳዩ ይበልጥ ግንዛቤ ከሚፈጥሩ ፊልሞች ውስጥ ጥቂቶቹ ላይ አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡

ድፍረት ፊልም

ድፍረት በአቶ ዘረሰናይ ብርሃነ መሐሪ የተሰራ የኢትዮጵያ ፊልም ነው። እ.ኤ.አ በ2014 ለእይታ የበቃው ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይዘቱም በጠለፋና መደፈር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ሜሮን ጌትነት፣ ራሄል ተሾመና ሌሎችም ተሳትፈውበታል።  አንጀሊና ጁሊና ጁሊ ምህረቱ የፊልሙ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች ቢሆኑም፤ የትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጁሊ ምሕረቱ አስተዋጽዖ በፊልሙ ላይ የጎላ ነበር፡፡ ይህ የሀገራችን ፊልም በሎስ እንጀለስ የሰንዳንስ ሽልማት ለማግኘትም የበቃ ነው፡፡

የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ዘረሰናይ ብርሃነ “ፊልሙን ስሰራ የጠለፋ ልማድን ለመናገር ነበር፡፡ ጥናት ሳደረግ በሁሉም የሀገራችን የጠለፋ ልማድ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪኩን በቦታ ለመወሰን አልፈለኩም” ሲል በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር፡፡

ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሚያጠነጥነው አስገድዶ የደፈራትን የ29 ዓመት ወጣት በገደለችው የ14 ዓመት ታዳጊ አበራሽ በቀለ (በፊልሙ ሒሩት) ሕይወት ዙሪያ ነው፡፡ ደፋሪዋ ሕፃኗን በጠለፋ ሊያገባትም ሙከራ አድርጐ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች እና በኋላም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ጉዳዩን ሰምተው ጥብቅና ቆመውላት “ራስን ለመከላከል” በሚል በነፃ እስከ ተለቀቀችበት ጊዜ ድረስ፣ አበራሽ በግድያ ክስ ተመሥርቶባት ማረሚያ ቤት ነበረች፡፡ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባትን ሴት ታሪክ የሚተርከው ፊልሙ ለተመልካቾች ስለሴት ልጆች ጥቃት ግንዛቤ የሚፈጥርና ጉዳዩን በጥልቀት ልብ እንዲሉት የሚያደርግ ነው፡፡

እ.ኤ.አ 64ኛ የበርሊን የፊልም አውደ ርእይ ላይ ከ400 በላይ ፊልሞች ለተመልካቾች ቀርበው ታይተዋል። በወቅቱ ለእይታ ከበቁ ፊልሞች መካከል ድፍረት ፊልም አንዱ ነበር፡፡

ችልድረንስ ኦፍ ዘ ሚስት

የ13 ዓመቷ ልጃገረድ ዲይ በሰሜን ቬትናም ጭጋጋማ ተራሮች ውስጥ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ተወለደች፡፡ ህይወቷም፣ የዕለት ተዕለት ኑሮዋም እንደ አካባቢው ሴት ልጆች ነበር፡፡ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ትሰራለች፤ ወደ ትምህርት ቤት ትሄዳለች። ነገር ግን አንድ ቀን ተጠለፈች፡፡ ችልድረንስ ኦፍ ዘ ሚስት በዚህች ልጃገረድ ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 ለእይታ የበቃው በዚህ ፊልም ላይ እንደሚታየው ታዳጊዋ ትምህርቷን አቋረጠች፡፡ በጠለፋ ትዳር ውስጥ ህይወትን መግፋት የያዘችው ዲይ ህይወቷ የበለጠ ሲወሳሰብ ፊልሙ ያሳያል፡፡ የዚህ ጾታዊ ጥቃት ውጤት በቤተሰብ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ሲደርስም ያሳያል፡፡

ችልድረንስ ኦፍ ዘ ሚስት ፊልም

ይህ ፊልም ልዩ፣ በማይታመን ሁኔታ የተሞላ አስተወሎት የተላበሰ እና ማህበረሰቡ የሴት ልጅ ጥቃትን እንዲከላከል የሚያነሳሳ ወኔ ቀስቃሽ ተብሎ መደነቁን ዘ ፒክስል ፕሮጀክት የተባለው ገጸ-ድር እ.ኤ.አ በ2022 የሰራው ዘገባ ያሳያል፡፡

የፊልሙ ዳይሬክተር ዲም ሃሊ “በፊልሙ ላይ በጥንታዊ ልማዶች እና በዘመናዊ እሴቶች መካከል ያለውን ግጭት፣ የሴቶች ጥቃትና መቆም ስላለበት ድርጊት ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በወጣቷ ልጅ ህይወት ውስጥ ስላጋጠሟት ፈተናዎች በማጉላት እና ልብ በሚነካ አቀራረብ በማሳየት ማህበረሰቡ ጉዳዩን ልብ እንዲለው ለማድረግ  ጥረት አድርጌያለሁ” ሲል ተናግሯል።

ድራይ

ድራይ የተሰኘው ፊልም የተሰራው በአፍሪካዊቷ ሀገር ናይጀሪያ ነው፡፡ ፊልሙ በልጅነታቸው ስለሚዳሩ ሴት ልጆችና ስለሚያስተናግዱት የህይወት ሰቆቃ የሚተርክ ነው፡፡ ፊልሙ ለእይታ የበቃው እ.ኤ.አ በ2014 ሲሆን፤ በስቴፋኒ ኦኬሬኬሊነስ ዳይሬክት የተደረገ እና በእውነተኛ የህይወት ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ድራይ ፊልም በሙሉ የሴቶች የልጅነት ጋብቻና ተጽዕኖው ላይ ያተኮረ ነው። ፊልሙ የ12 ዓመቷን ታዳጊ ሃሊማ (በፊልሙ ላይ ዙበይዳ ኢብራሂም ፋጌ) ታሪክን መነሻ በማድረግ የተሰራ ነው፡፡ ሃሊማ ሚስት ብሎ ባገባት ጎልማሳ መደፈሯን፣ በዚህም የኖረችበትን አስከፊ ህይወት፣ የስነልቦና እና የአካል ጉዳት ይተርካል። ፊልሙ የ12 ዓመት ልጃገረድን ለ60 ዓመት አዛውንት መዳር እንዴት ትዳር ሊባል ይችላል ሲል ይጠይቃል፡፡

ድራይ ከተሰኘው ፊልም የተወሰደ

ይህ ፊልም  ከመልዕክቱ በተጨማሪ ልዩ የሲኒማቶግራፊ እውቀት እና ፈጠራ የታከለበት ስራ ተብሎ መወደሱን ሲቲዝን ግሎባል ገጸ ድር እ.ኤ.አ በ2021 “7 African Movies That Highlight the Dangers of Gender-Based Violence” በሚል በሰራው ዳሰሳ ላይ ገልጿል። ፊልሙ ለናይጄሪያዊያን ሴቶች ነፃነት በመቆም ግንባር ቀደም ሆኖ ተቀምጧል።

በአጠቃላይ ከላይ የተሰሩትን ፊልሞች ለአብነት ጠቀስን እንጂ የሴቶች ጥቃት ላይ የተሰሩ ፊልሞች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በግብጽ የተሰራውን ዘ ቺልድረን ኦፍ ናይል፣ በሶማሊያ የተሰራው ኤ ገርል ፍሮም ሞቃዲሾ፣ በላይቤሪያ የተሰራው አናዘር ዋር፣ በህንድ የተሰራው ፒንክ እና በቱርክ የተሰራውን ዳይንግ ቱ ዳይቮርስን ለአብነት መዘርዘር ይቻላል፡፡

በመሆኑም በፊልሞች አማካኝነት የሴቶችን ጥቃት ለማስወገድ የሚያስችሉ መልእክቶችን ማስተላለፍና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ናኩሃንያ ንግኮፖ የተባሉ ምሁር እ.ኤ.አ በ2015 በሰሩት ጥናት ፊልም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶችን አጉልቶ በማውጣት እና በመተቸት መፍትሄ እንዲገኝላቸው የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ ነው። በዚህም የፊልሙ ተመልካቾች በትምህርት ቤት እና ማህበረሰቡ ውስጥ የፆታ ጥቃት ጉዳዮችን ልብ እንዲሉ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው እና የማህበረሰቡ ግንዛቤ ከፍ እንዲል ትምህርት ይሰጣል ይላሉ፡፡ አጥኝዋ ይህ ስራ በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ውጤት ማምጣቱን በጥናታቸው አትተዋል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review