የሴኔጋል ሴቶች የአየር ንብረት ለወጥ ፍትኃዊነትን የሚጠይቅ ሰልፍ አካሄዱ

  • Post category:ዓለም

AMN-ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም

በቅርቡ በአዘርባጃን ከሚካሄደው የኮፕ 29 ወይም ከተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ አስቀድሞ የሴኔጋል ሴቶች የአየር ንብረት ለወጥ ፍትኃዊነትን የሚጠይቅ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

በሰልፉ 50 ሴት የማህበረሰብ አንቂዎች የተሳተፉ ሲሆን በሀገራቸው ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ በዳካር ጎዳናዎች ላይ ባካሄዱት ሰልፍ አስታውቀዋል፡፡

በተለይም ቀጣዩ ዘመን ከካርበን ልቀት የፀዳ እንዲሆን ነው ሴቶቹ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

ከማህበረሰብ አንቂዎች መካከል አንዷ የሆነችው ቼይክህ ኒያግ ፋዬ ለአራት አመታት ተመሳሳይ ሰልፍ ያደረግን ቢሆንም ምንም አይነት ለውጥ አላየንም ትላለች፡፡

ከኢንዱስትሪው በሚለቀቁ ጋዞች ምክንያት የዓለም ሙቀት በእጅጉ መጨመሩን የምትናገረው ፋዬ ይህ በተለይም በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችን እየጎዳ እንደሚገኝ ገልጻለች፡፡

እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2024 በሴኔጋል ታሪክ ከፍተኛ የተባለለት የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

የተከሰተው ጎርፍ በሰሜንና ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የለማ ሰብልም አውድሟል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የካርበን ልቀትን ለመቀነስና ለመከላከል ከሰሩ አህጉሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የምትከፍለውን ዋጋ ያስቀራል ብለዋል ሴቶቹ፡፡

የሰልፉ አስተባባሪ የሆነችው እና የዳካሯ ማህበረሰብ አንቂ ካማራ በበኩሏ፣ በዚሁ ወር ከሚካሄደው የአዘርባጃኑ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ጎን ለጎን ሀገራት የፓሪስን ስምምነት ሊያከብሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርባለች፡፡

“አሁን አየር በካይ የሆኑ የካርበን ጋዝ የሚለቁ ሀገራት ይህን ተግባራቸውን ለመቀነስ የሚስማሙበት ጊዜ ነው፤ አፍሪካ ዋጋ እየከፈለች ያለችው በዚሁ ምክንያት ነው ” ስትል አስተባባሪዋ ማሳሰቧን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review