ዜጎች ሰርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገርን ለመለወጥ በተለያዩ ሀገራት ተንቀሳቅሰው መስራት የተለመደ ነው። በርካታ ዜጎች ከሄዱባቸው መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ ሀገራት በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ላይ ከእውቀት እና ክህሎት ክፍተት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥማቸው ነበር። መንግስት በውጭ ሃገር የሚሰማሩ ዜጎች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ በሚሰሩት ሙያ መሰልጠን እንዳለባቸው በማመን የሙያና ክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ እያደረገ ይገኛል፡፡
ወጣት ሙሉዋ ፍቅር ትምህርቷን እስከ አስረኛ ክፍል ተምራለች፡፡ ሆኖም ከዚህ በላይ ለመቀጠል ውጤት ሊመጣላት ባለመቻሉ በወጣትነቷ ያለ ስራ መቀመጥ እንደሌለባት በማመን መንግስት በውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ባመቻቸው እድል ተጠቅማ ራሷን ለመለወጥ መወሰኗን ገልፃልናለች፡፡
ወጣቷ ለውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት የሚያግዛትን ስልጠና በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ በምግብ ዝግጅት፣ በልብስ እጥበት፣ በቤት አያያዝ፣ በስራ መሃል ስለሚኖር መልካም ግንኙነትና ሌሎችም እየሰለጠነች ካለችባቸው መካከል መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

“ስልጠናው የምሰማራበት የስራ መስክ አዲስ እንዳይሆንብኝ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ ስራ እንድሰራ የሚያስችለኝ ነው። ጥሩ እውቀት አግኝቼበታለሁ፡፡ ይህን እድል በማግኘቴም ደስተኛ ነኝ፡፡ ኮሌጁ በነፃ እያሰለጠነኝ ነው። ላደረገልኝ ድጋፍ አመሰግናለሁ፡፡ መንግስትም እንዲህ አይነት እድል ፈጥሮልን በሰለጠንነው ሙያ እንድንለወጥ እገዛ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ እኔም ከኮሌጁ ባገኘሁት ስልጠና ያለኝን ክህሎት አዳብሬ ሰርቼ ለመለወጥ እተጋለሁ” ብላለች ወጣት ሙሉዋ፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለውጭ ሀገር የስራ ስምሪት የሚሄዱ ወጣቶች በእውቀት የበለፀጉ እና ያላቸውን ክህሎት በስልጠና አዳብረውና ብቁ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በተለያየ ሙያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናው ወጣቶቹ ክህሎታቸውን አዳብረው በስራቸው ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሁም ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን በኮሌጁ የሆቴልና ቱሪዝም ዲፓርትመንት ተጠሪ አሰልጣኝ ጅብሪል ነጋሽ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ ገልፀዋል፡፡
አሰልጣኝ ጅብሪል፤ ዜጎች በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ዘርፍ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው በቅድሚያ መሰልጠን ስላለባቸውና ስልጠናው በኮሌጅ መሆን እንዳለበት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ኮሌጁ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በተለያየ ሙያ ለ21 ቀናት እንዲሰለጥኑ እያደረገ ይገኛል፡፡ ስልጠናው የሚሰጠው በአራት ዘርፎች በምግብ ዝግጅት፣ በልብስ እጥበት፣ በምግብና መጠጥ መስተንገዶ እንዲሁም በቤት አያያዝ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአረብኛ ቋንቋም እንደሚማሩ ገልፀዋል፡፡
እንደ አሰልጣኝ ጅብሪል ገለፃ፣ ስልጠናው የሚሰጠው ከክፍያ ነፃ ሲሆን በአራቱም ሙያዎች መጀመሪያ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን ይማራሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በአብዛኛው የተግባር ስልጠናውን ይወስዳሉ። ከተግባር ስልጠናው በኋላ ሰልጣኞች ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) እንዲመዘኑ ይደረጋል፡፡ ምዘናውን በኮሌጁ በተግባር እንዲመዘኑ ከተደረገ በኋላ ወደ ስራ ስምሪት ይሄዳሉ፡፡
ኮሌጁ ከዚህ ቀደምም ውጭ ሃገር ለስራ ለሚሄዱ ዜጎች ስልጠና የመስጠት ልምድ አለው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመንግስት በኩል ለሚመጡ ሰልጣኞች ለውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ዘርፍ ስልጠና መስጠት ላይ የበኩሉን ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛል። በዚህም በአንደኛው ዙር 20፣ በሁለተኛው ዙር 27 ወጣቶችን አሰልጥኗል። በአሁኑ ወቅትም ከአራዳ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የተላኩ ወጣት ሙሉዋን ጨምሮ 68 ወጣቶች በምግብ ዝግጅት፣ በልብስ እጥበት፣ በምግብና መጠጥ መስተንግዶ፣ በቤት አያያዝ ዘርፎች ለውጭ ሃገር የስራ ስምሪት እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አልፎ ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት መብትና ግዴታቸው ምን መሆን እና ምን መስራት እንዳለባቸው፣ በሰዎች መካከል ስላለው መልካም ግንኙነት እንዲያውቁና ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ ይህ የስልጠናው አንድ አካል ተደርጎ እንደሚሰለጥኑ አሰልጣኝ ጅብሪል አስረድተዋል። ኮሌጁ በቀጣይም ውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ለሚሄዱ ዜጎች የሚሰጠውን የስልጠና አገልግሎት አጠናክሮ በመቀጠል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።የዲፓርትመንቱ ተጠሪ እንዳስረዱት፣ የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት ለሚሄዱ ዜጎች ስልጠናው በኮሌጅ ደረጃ መሰጠቱ ጥቅም አለው። ይህም ኮሌጁ ባለው እምቅ አቅም መሰልጠን የሚገባቸውን ስልጠና በአግባቡ እንዲሰለጥኑ ስለሚያደርግ በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል። እንደሃገርም የሰለጠነና የተመዘነ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ወደ ውጪ ለመላክ በሚደረገው ጥረት በአግባቡ ስልጠና የወሰዱትን ለመለየት እንዲሁም ሰልጥነው የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት የስራ እድል የተፈጠረላቸውን ለማወቅ ጥቅም እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
ሰልጣኞች ሀገር ውስጥም ሆነ ውጭ ሃገር ለስራ ስምሪት ሲሄዱ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ሙያ የራሱ የሆነ ክህሎትን የሚጠይቅ በመሆኑ በስልጠናው መሰረት ትኩረት ሰጥተው ወደ ተግባር መቀየር አለባቸው፡፡ መብትና ግዴታቸውን አውቀው መስራትና መለወጥም ይገባቸዋል ሲሉም ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። የጋዜጣው ዝግጅት ክፍልም በኮሌጁ ለውጭ ሃገር የስራ ስምሪት በተለያየ ሙያ እየሰለጠኑ የሚገኙ ወጣቶችን ተዘዋውሮ ቃኝቷል፡፡ በልብስ እጥበት ዘርፍ በተለያዩ ዘመናዊ የልብስ ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽኖች አማካኝነት የልብስ አስተጣጠብ፣ አተኳኮስ፣ አቀማመጥ ስልጠናን በኮሌጁ አሰልጣኝ ሲሰጣቸው ለመመልከት ችለናል፡፡
እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከሚሰጠው የስልጠና አገልግሎት ባለፈ ዜጎች በተለያየ ሙያ ሰልጥነውና ስኬታማ ስራ ሰርተው እንዲለወጡ በነፃ ማሰልጠኑ ለዜጎች ተጠቃሚነት ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የሚበረታታና ዓርአያ የሚሆን ተግባር በመሆኑ በዚሁ ይቀጥል። መንግስትም ዜጎች በመረጡት ሙያ የስራ እድል ተጠቃሚነታቸው እንዲሰፋ ለማድረግ ሰልጥነውና የሙያ ባለቤት ሆነው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል እያደረገ ያለው ተግባር በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ ይህ መልካም ክንውን ሊቀጥል ይገባል እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው