“ህብረተሰቡ ለሽግግር ፍትሕ ሥራው ሁነኛ የመረጃ ምንጭነቱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል”
የሕግ ባለሙያ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ
የሠው ልጅ ድንቅ ፍጡር ነው፡፡ በተፈጥሮ ላይ ገዢ የሚያደርገውን ፀጋ ተላብሷል፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አስደናቂ ሥራዎችን እያከናወነ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ምን ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል፤ እያሳየም ይገኛል፡፡ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ተደጋግሞ የሚገለፀውን፤ “ጥረህ ግረህ ብላ” ትዕዛዝ ወይም ኃላፊነት ለመወጣት ሠው የሆነ ፍጡር በየዕለቱ ይተጋል፤ ይታትራል። ሠዋዊ ባህሪ ነውና፤ በተቃርኖ የታጀበ ሕይወትንም ይመራል። መወለድ እና መሞትን፣ መጋጨት እና መታረቅን፣ መደሰት እና ማዘንን፣ መታመም እና መዳንን … የሕይወቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች አድርጓቸው እየኖረ ነው። እነዚህና መሰል ሠዋዊ መገለጫዎች በግል ብቻ የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ወደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና ሀገር ያድጋሉ፤ ይሰፋሉ፡፡
ምድርን አርሶ፣ ባህርን ሰንጥቆ፣ ወደ ጠፈር መጥቆ ውስጠ ገመናቸውን እስከመግለጥ የሚደርስ እና ከዚህም የሚያልፍ ልዩ ተፈጥሮ የተቸረው ሠው፤ ደህናውን ከመጥፎ፣ ጠቃሚውን ከጎጂው …መለየት አቅቶት ለውድቀትና ለችግር ሲዳረግ መመልከትም የተለመደ ነው። ከሠላም ይልቅ ጦርነትን፣ ከእርቅ ይልቅ ፀብን፣ ከልማት ይልቅ ጥፋትን፣ ከዕድገት ይልቅ ውድቀትን … የመምረጥ እና የመከተል “አባዜ” ሠውኛ መገለጫ ሆኖ በዚህ ዘመንም ቀጥሏል። በእኛም ሀገር ይኸው ሠዋዊ ተፈጥሮ በዘመን ዑደት ውስጥ እየፈሰሰ እዚህ ደርሷል። በተለይ ግጭት፣ ጦርነት፣ ርሃብ፣ ኋላቀርነት፣ ድህነት የመሳሰሉት አሜኬላዎች ደጋግመው የሚጎበኙን ቤተኞች አድርገናቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ከእኛው ከውስጣችን የሚመነጭ ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡
ባለፉት ጊዜያት በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱት አለመግባባቶች፣ ቅራኔዎች፣ ግጭቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል፣ ለንብረት ውድመት፣ ለአካል ጉዳት እና ለሞት ዳርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ለዘመናት የዳበሩ የአብሮነት እና የመቻቻል እሴቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
በሀገር እና በሕዝብ ላይ ሲደርስ የቆየውን አስከፊ ውጤት መቀልበስ፣ ማረምና ማስተካከል ይቻላል፡፡ የተሳሳተውን መንገድ ትተን የእውነት፣ የዕርቅ፣ የምህረት እና የፍትሕ መርህን ከተከተልን ያማረ ፍሬ እንሰበስባለን፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሀገር ሲከሰቱ ለቆዩት ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ይቻል ዘንድ፤ የሽግግር ፍትሕ የሚያስገኝ ሀገራዊ ፖሊሲ፣ አሠራር እና አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ተግባር የተገባው፡፡ ይህን የሽግግር ፍትሕ በአግባቡ መፈፀም ከተቻለ የኢትዮጵያ መከራ አብቅቶ ትንሳኤዋ ዕውን ይሆናል። እዚህ ጋ “ትንሳኤ” የሚለውን ቃል ያነሳነው የሀገር መዳኛ የመሆን አቅም ያለውን የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ከትንሳኤ በዓል ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምስጢር ጋር አሰናስለን ብንመለከተው ጥሩ ይሆናል በሚል ነው፡፡
አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ይባላሉ። የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ባለፉት ጊዜያት በተለይም፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ፖለቲካዊ ቅራኔዎች ተፈጥረዋል። ሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲደራጁ፣ አቅም እንዲፈጥሩ እና በሕዝብና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ ፖለቲካዊ ጫናዎች በሕገወጥ ቡድኖች አማካኝነት ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ፤ “አንተ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለህም፤ የዚህ ክልል ባለቤት አይደለህም፤ ለቀህ ውጣ” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ግጭቶች እንዲፈጠሩ እና ብዙዎች ከፍተኛ ሠብዓዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው አድርጓል፡፡ ይህንን ለዓመታት የዘለቀ ቅራኔና ችግር ለመፍታት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዓይነተኛ መሣሪያ ወይም ወሳኝ የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡
“እንደ ሀገር የተከሰቱ እና እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ተያያዥ ችግሮች እንዳይከሰቱ እንደ ልጓም ሆነው ሊገቱ ለሚችሉ አራት ወሳኝ ነገሮች ማለትም፦ ለፈጣሪው (ለዕምነቱ)፣ ለማህበረሰቡ፣ ለሕግ እና ለራሱ (ሕሊናው) ተገዢ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለአራቱ መገዛት ባይችል፤ ቢያንስ ለአንዱ ተገዢ ይሆናል። እንደ ሀገር እና ሕዝብ የተፈጠረውን እና እየተፈጠረ ያለውን ጥፋት ስንመለከት የሠው ልጅ በጋራ ለመኖር የሚያግዙ ቁልፍ እሴቶችን የጣሱ ሆነው እናገኛቸዋለን” ያሉት አቶ ጥጋቡ፤ የተሳሳተ አመለካከት ይዞ በሕዝብ እና በሀገር ላይ ጉዳት እንዲከሰት የሚያደርግ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን እኩይ ተግባሩ ተቀባይነት የማያገኘው በእምነት መርህ ሚዛን ተሰፍሮ ብቻ ሳይሆን፤ በሕግ እና በሞራል መለኪያም ከጥፋተኛነት እንደማይድን ተናግረዋል፡፡
የሽግግር ፍትሕ መሰረታዊ ዓላማዎች፦ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ተበዳዮችን መካስ እና መልሶ ማቋቋም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ ተመሳሳይ ችግር ወይም አደጋ እንዳይከሰት፣ ሠላምንና ደህንነትን በዘላቂነት ማስፈን፣ በሕግ የበላይነት የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠር፣ የተረጋጋ ፖለቲካዊ አስተዳደር መገንባት፣ በሕዝብና በመንግስት መካከል መተማመንን ዕውን ማድረግ ከሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መተግበር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህን እንደ ሀገር እና ሕዝብ የምንመኛቸውን ዓላማዎች (ተጠባቂ ውጤቶች) እውን ለማድረግ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የሕግ ሰነዱ ወደ ውጤት መውሰጃ መንገድ እንጂ በራሱ ውጤት አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ ሌሎች የሕግ ሰነዶች ሁሉ፤ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ ውስጥ ቁልፍ ሃሳቦችን የተሸከሙ ቃላትን እናገኛለን። ከእነዚህ መካከል፤ ጥፋት፣ እርቅ፣ እውነት፣ ማካካሻ (ካሳ)፣ ፈውስ የሚሉት መጋቢት 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ “የቃላት እና ሐረጋት ፍቺ” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ሰፍረው እንመለከታቸዋለን። እነዚህን ቃላት የትንሳኤ በዓልን ሃይማኖታዊ ምስጢር ለማስረዳት በተዘጋጁ ፅሑፎች ውስጥ በተደጋጋሚ እናገኛቸዋለን፡፡ ጥፋት (ኃጥያት)፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ መስዋዕትነት (ቤዛነት)፣ ምሕረት (ድህነት) የመሳሰሉት ቃላት ሃይማኖታዊውን አስተምህሮ ለምዕመናኑ ለማስረፅ በወሳኝነት ጥቅም ላይ ውለዋል።

በክርስትና ዕምነት ተከታዮች በታላቅ ክብርና ድምቀት የተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል፤ ትርጉሙ ጥልቅና ሰፊ መሆኑን በእምነቱ አስተምህሮ ተደጋግሞ ይገለፃል። በዓሉን በታላቅ ደስታ እና ሕብረት የሚያከብሩት፤ “በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል። ሙታን የነበርን ሕያዋን፤ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን፤ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል” የሚለውን ሀይማኖታዊ ቃል ምክንያት በማድረግ መሆኑን ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው ከሁለት ዓመት በፊት ለንባብ ባበቁት ፅሑፍ ገልፀዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ፤ በዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት፣ ደስታ፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ ተከብሯል፡፡ የበዓሉን ታላቅነት ከትንሣኤው በፊት የሚያልፉት ከባድ ጊዜያት ያጎሉታል። ከበዓለ ትንሣኤ በፊት ምዕመናኑ፤ ሁለት ወራት ለሚጠጉ ቀናት በፆም፣ በፀሎት እና በስግደት ይቆያሉ፡፡ በመጨረሻው ሳምንት ባሉት ቀናት (የሰሙነ ሕማማት ዕለታት) ፆም፣ ፀሎቱ እና ስግደቱ ይበረታል፡፡ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ የሚቆዩት የሰሙነ ሕማማት ዕለታት የየራሳቸው ስያሜና ትርጉም እንዳላቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አቡቀለምሲስ ሚዲያ ገፀ ድር ላይ ከአራት ዓመታት በፊት፤ “ስቅለት፡ ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ሰቀሉት” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በሠፈረው ፅሑፍ ውስጥ ተብራርቷል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ትንሣኤን አጥብቀው ይሻሉ፡፡ መሻታቸው ዕውን እንዲሆን ደግሞ በሽግግር ፍትሕ ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል፡፡ የተስፋቸውን ፍሬ ለማፈስ፣ ከትንሣኤውም ለመድረስ መንገዱ ቀላል እንደማይሆን ሊረዱ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የሽግግር ፍትህ የያዛቸውን መሰረታዊ ዓላማዎች ማለትም፡- እውነትን መፈለግ እና ማወቅ፣ የተጎዱት ሰዎችን መልሶ ማቋቋም፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዲሁም ተመሳሳይ ነገር ዳግም እንዳይከሰት ማስቻል የሚሉት ይገኙበታል። ይህንን ዓላማ ለማሳካት ቀላል የማይባል ሥራን ይጠይቃል፡፡
“በሀገራችን ሕዝብ ሁሌ ፋሲካ የለም የሚለው አባባል የበዓሉን ዋጋ ከፍተኛነት ለመመስከር ይመስላል፡፡ ከበዓሉ አስቀድሞ የሚከፈል ዋጋ አለ፡፡ በተሳሳተ መንገድ የተጓዘው አዳም፣ የፈጣሪውን ትዕዛዝ የሻረው አዳም፣ በኃጢያት የወደቀው አዳም፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ የተወረወረው አዳም … የሠውን ልጅ ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለውን ከፍተኛ ዋጋ፤ በቤተልሔም የተጀመረው የሰውን ልጅ የማዳኑ ሥራ የተጠናቀቀበት፣ ጌታም ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ ሠርቷል” በማለት የሚገልጸው መረጃው፣ የቤዛነት ሥራ የተከናወነበት ዕለትም፤ ዕለተ ዓርብ (የስቅለት ዕለት) መሆኑን በማስታወስ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የተባለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የተፈጸመበት ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ውጤታማ እንዲሆን መደረግ ስላለበት ጉዳይ የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ የሚከተለውን ብለዋል፤ “ሕግ ጉልበትም ውጤትም የሚኖረው ቅንጅታዊ አሠራር መስፈን ሲችል ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ውጤት መዳረሻው መንገድ በትክክል ዓላማውን እንዲያሳካ ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጀምሮ ወሳኝ ኃላፊነት ያለባቸው ሁሉ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ሥራ በቅንጅት የሚከናወን ነው፡፡ ጥፋቶች እና በደሎች፣ አጥፊዎችና ተበዳዮች በትክክል መለየት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ‘ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚደበቅ ነገር የለም’ እንደሚባለው፤ ህብረተሰቡ ለሽግግር ፍትሕ ሥራው ሁነኛ የመረጃ ምንጭነቱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን በአዋጅ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፌደራል ፖሊስ፣ መረጃ ሰጪ ተቋማት ከላይ እስከ ታች ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው፡፡ የክልል መስተዳድሮች በክልላዊ አስተዳደሮቻቸው ስለተፈፀሙ ጥፋቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚደረገው የምርመራ ሂደት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዕምነት ተቋማት የማይተካ ሚናቸውን በአግባቡ መፈፀም ይኖርባቸዋል፡፡ የዕምነት ተከታዮችን ወደ አማኝ ደረጃ ማምጣት ይገባል፡፡ የሠው ልጅ ሊጋራው የሚገባውን የወንድማማችነት፣ የእህትማማችነት፣ የአንድነት እና የህብረት መንፈስን በየዕምነቱ ተከታዮች ማስረፅ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
በደረጀ ታደሰ