የሸክላ ሙዚቃዎች ውለታ

You are currently viewing የሸክላ ሙዚቃዎች ውለታ

እጅግ በከፍተኛ ደረጃ እየዘመኑ ያሉ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች ህይወትን ከማቅለል አንስቶ ዘርፈ-ብዙ አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው፡፡ ለአብነትም ሙዚቃን ብንወስድ ዛሬ ላይ በቀላሉ በያዝነው የእጅ ስልክ አማካኝነት ስንፈልግ ገዝተን፤ ስንፈልግ የኢንተርኔት ዳታ ተጠቅመን ሙዚቃን ማጣጣም እንችላለን፡፡ ይሁንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንደአሁኑ ሳይራቀቅ በፊት የሙዚቃ የዕደገት ጉዞ ከሸክላ ህትመት እስከ ዲጂታል ዘመን ብዙ ውጣ ውረዶችን ለማለፍ ተገድዷል። በዚህ ጽሁፍም በየዓመቱ በፈረንጆቹ ጥቅምት 27 ቀን ማለትም በነገው እለት በመላው ዓለም የሚከበረውን የዓለም የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርስ ቀንን መነሻ በማድረግ የሸክላ ሙዚቃዎች ውለታና ታሪክ በአጭሩ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

የሸክላ ሙዚቃዎች በሙዚቃ ዕድገት ውስጥ ትልቅ አበርክቶ አላቸው

 የኦዲዮ-ቪዥዋል ቀን ለምን ይከበራል?

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በይፋዊ ገጸ-ድሩ ነገ የሚከበረውን የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርስ ቀንን አስመልክቶ ባሰፈረው ጽሁፍ፣ የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርሶች ከመላው አለም ስለሰዎች ህይወት፣ ባህል፣ ዕሴትና ታሪኮቻቸውን ብዙ ይነግሩናል፣ ያስተምሩናልም ሲል ገልጿል። የማህበረሰቡን ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና የቋንቋ ብዝሃነት ስለሚያንፀባርቁ የጋራ ትውስታችን መገለጫ እና ጠቃሚ የእውቀት ምንጮችም ናቸው ይላል፤ መረጃው፡፡ የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርሶች በዋጋ የማይተመን ትልቅ ፋይዳ አላቸው የሚለው የዩኔስኮ መረጃ፣ ሁላችንም የምንጋራውን ዓለም እንድታድግ፣ የእርስ በእርስ መስተጋብራችን እንዲጎለብት እና እንድንረዳዳ ትልቅ ሚና አላቸው። በዚህም የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርሶችን በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ ተደራሽ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ዩኔስኮ በአጽንኦት ያሳስባል፡፡ የዩኔስኮ ቤተ-መዛግብትም ይህንን ዓላማ ዕውን ለማድረግ “የጋራ የዩኔስኮ ታሪካችንን ዲጂታል ማድረግ” የሚለውን ፕሮጀክት መጀመሩንም በመረጃው አክሏል፡፡ በአጠቃላይ የዓለም የኦዲዮ-ቪዥዋል ቅርስ ቀን በዋናነት የቆዩ የድምጽ ቅጂዎችንና ምስሎችን መጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል ይበልጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው በየዓመቱ የሚከበረው፡፡

የሸክላ ሙዚቃዎች ከትናንት እስከ ዛሬ

በፈረንጆቹ 1877 አንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ፈጠራ በአሜሪካዊው ሳይንቲስት በቶማስ ኤዲሰን አማካኝነት ዕውን ሆነ፡፡ ቶማስ ኤዲሰን የፈለሰፈው አዲሱ ግኝት “ፎኖግራፍ” ይሰኛል፡፡ ኤድሰን የፈጠረው ፎኖግራፍ በዋናነት የሰዎችን ድምጽ መቅረጽና በድጋሚ ማሰማት የሚችል መሳሪያ ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ግን ፎኖግራፍ አሠራሩ በጣም ተሻሽሎ ድምጾችን በሙዚቃ ሸክላ ላይ ወደ መቀረጽ አደገ፡፡ ለዚህ ወሳኝ ዕድገትና ፈጠራ ባለቤት ደግሞ አሜሪካዊው ሳይንቲስት ኤምል በረሊንር ነው፡፡ በረሊንር በፈረንጆቹ 1894 በሸክላ ዲስክ ድምጽን መቅረጽና ማተም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሲያስተዋውቅ ብዙ የሙዚቃ ስራዎች ለመቅዳትና ለማተም  ጥሩ ዕድሎችን ፈጠረ። የሙዚቃ ሥራዎችም ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ለብዙዎች መዳረስም ጀመረ፡፡

ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃዎቻቸው በሸክላ የተቀረፁላቸው ኢትዮጵያዊ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ናቸው፡፡ የነጋድራስ ተሰማ ሙዚቃዎች በሸክላ የተቀረጹት ጀርመን ውስጥ ሲሆን ጊዜውም በሀገራችን አቆጣጠር በ1902 ዓ.ም እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ1900 ዓ.ም ወደ ጀርመን ለትምህርት የሄዱት ነጋድራስ ተሰማ ቀድሞ በሀገራቸው ማሲንቆ መምታትና ዜማ ተምረው ስለነበር፣ ከጀርመኑ ፒስ ማስተርስ ቮይስ ከተባለ ኩባንያ ጋር በመዋዋል 17 የሸክላ ዲስክ ሙዚቃዎችን ለማሳተም ችለዋል፡፡ የልጅ ኢያሱ የቅርብ ወዳጅ የነበሩትና የታላቁ የስፖርት ሰው የይድነቃቸው አባት የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በሸክላ የተቀረጹ የሙዚቃ ስራዎቻቸው ኋላ ላይ በኢትዮጲክስ ቁጥር 27 የሙዚቃ ሲዲ ውስጥ ታትሞ እንደገና ለአድማጭ ቀርቧል፡፡ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የሙዚቃ ስራዎች የተጀመረው የሸክላ ሙዚቃ ህትመት፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሌላው ስለ ኢትዮጵያ የሸክላ ሙዚቃዎች ሲነሳ ስሙ አብሮ የሚነሳ አንድ ሰው አለ፤ ሙዚቃ አሳታሚና አከፋፋይ አምሃ እሸቴ። አምሃ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሀገራችን  በግለሰብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሸክላ ሙዚቃ ህትመት የጀመረውና ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገው አምሃ እሸቴ ነው፡፡ እስከ 1960ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ሙዚቃ በብቸኝነት የሀገር ፍቅር ማህበር ያሳትም እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ውለታ የዋለው አምሃ እሸቴ ከዚያ በፊት በግለሰብ ደረጃ ያልተለመደውን የሸክላ ሙዚቃ ህትመት ነው በ1960ዎቹ አጋማሽ የጀመረው፡፡ ይሄ ጅማሮ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ፍራንሲስ ፋልሴቶ ያሳተማቸው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የኢትዮጲክስ ሙዚቃ ስብስብ ስራዎች ውስጥ የአቶ አምሃ እሸቴ ቀደምት የሸክላ ሙዚቃ ህትመቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ይመስላል ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር ገጸ-ድር በፈረንጆቹ ግንቦት 7 ቀን 2023 ባስነበበው ጽሁፍ፣ “…በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በግለሰብ ተነሳሽነት ሙዚቃን በሸክላ ለማሳተም የደፈረው አቶ አምሃ እሸቴ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃን ካዘመኑት አሳታሚና አከፋፋዮች ግንባር ቀደሙ ሰው ነው” ሲል ነው አድናቆት የቸረው፡፡

የኢትዮጲክስ ተከታታይ የሙዚቃ ስብስቦች በ1989 ዓ.ም መውጣት ከመጀመሩ በፊት በሸክላ የታተሙ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ለምዕራብ አድማጮች ለማድረስ ጥረት ያደረገው ፈረንሳያዊው የሙዚቃ ተመራማሪውና የኢትዮጲክስ የሙዚቃ ስብስቦች አሳታሚ ፍራንሲስ ፋልሴቶ ነው፡፡ ፍራንሲስ ወርሃ የካቲት 2001 ዓ.ም ለወጣችው ለ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ እንደተናገረው፤ እ.አ.አ በ1978 በቤልጅየም ብራስልስ የመሃሙድ ሙዚቃ አንድ ሸክላ ታተመ፡፡ ይህ ሙዚቃ ወደ ምዕራባውያን ጆሮ ለመድረስ የመጀመሪያው ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን ይህ የሙዚቃ ሸክላ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ቻለ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች በውጭው ዓለም በስፋት መደመጥና ተወዳጅነትን ማትረፍ የጀመሩት። ከዚህ አንጻር የሸክላ ሙዚቃዎች አስተዋጽኦ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡

ሌላው የሚያስገርመው ነገር የሸክላ ሙዚቃ ህትመቶች ዛሬ ላይም እጅግ ተፈላጊ የመሆናቸው ምስጢር ነው፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎች ተሰቅለው ከምናነባቸው ማስታወቂያዎች መካከል የሸክላ ሙዚቃዎች ያሉበት ድረስ መጥተን እንገዛለን የሚል ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም እንደ ቲክቶክና ፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ ገጸ-ድሮች የሸክላ ሙዚቃዎችን ለመግዛት የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚያስነግሯቸው ማስታወቂያዎች መስማት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በእርግጥ የሸክላ ሙዚቃዎች አሁን ባለንበት የዲጂታል ዘመን ውስጥ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን አሜሪካና የአውሮፓ ሃገራትም ጭምር ነው፡፡

በአሜሪካ የሸክላ ሙዚቃዎች ከብዙ ዓመታት በኋላ ከሲዲዎች ሽያጭ መብለጡን ቢቢሲ በፈረንጆቹ መጋቢት 14 ቀን 2023 ባወጣው አንድ ጽሑፍ አስነብቧል፡፡ በዚሁ መረጃ መሰረት፣ በፈረንጆቹ 2022 ብቻ ከ41 ሚሊዮን በላይ የሸክላ ሙዚቃዎች የተሸጡ ሲሆን፤ በዚህም እስከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። በሌላ በኩል በዚሁ ዓመት የተሸጡ የሙዚቃ ሲዲዎች ከሸክላ ህትመት ያነሱ ናቸው። በዚህ መሰረት የተሸጡ የሙዚቃ ሲዲዎች 33 ሚሊዮን ሲሆን ገቢውም 483 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የሸክላ ሙዚቃዎች ተፈላጊነት ከፍ ያለበት ምክንያት የሙዚቃ አፍቃሪዎች በሸክላ ሙዚቃ ላይ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ድምጾች በማግኘታቸው እንደሆነም ቢቢሲ በዘገባው አክሏል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review