AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
ለኦነግ ሸኔ ሽብር ቡድን የሎጅስቲክስ ድጋፍ አቀባይ የነበረው ኤፍሬም ገብረ ስላሴ እና ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ከአዲስ አበባ እና አካባቢው የተለያዩ መጠቀሚያዎችን በማሰባሰብ በአሸዋ ሜዳ እና በሆለታ ከተማ በማቀባበል ወደ ሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ለማስተላለፍ በሚንቀሳቀሱበት ዕለት በፀጥታ ሀይሎች በተደረገ ክትትል ዓላማቸውን ሳያሳኩ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደቻለ ተገልጿል።
ከሰላም ወዳዱ ህዝብ በተገኘ ጥቆማ እና በፀጥታ ሀይሎች ብርቱ ክትትል መሰረት የሎጅስቲክስ አቀባዩ እና ግብረአበሮች ሀብታሙ ጫላ እና አብዲ ካሱ ተይዘው ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ከፖሊስ ጋር በመሆን በተደረገ ፍተሻ 2.010 የመትረየስ ጥይት ፣ 35 ጥንድ ከስክስ ወታደራዊ ጫማ እና የተለያዩ የፀጥታ ሀይሎች የደምብ ልብሶችን መያዝ መቻሉ ተመልክቷል።
በአሁኑ ጊዜ በሠራዊቱ የተጠናከረ ዘመቻ እየተመታ የሚገኘው የሸኔ ሽብር ቡድን ከአመራሮቹ ጀምሮ እጅ በመስጠት ላይ መሆኑንና ከሎጅስቲክስ አቀባዩ ጋር እና ከግብረ አበሮቹ ጋር ትስስር ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ላይ መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።