AMN – ጥር 13/2017 ዓ.ም
የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደተሀድሶ ስልጠና የማስገባቱ ስራ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ማዕከል ተጀምሯል።
በብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የብቃትና የሰው ሃብት ስራ አስፈፃሚና የዳባት ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ግዛቸው መኩሪያ፥ በትግራይ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሰላም አማራጭን የተቀበሉ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ሰላም እንደሚያስፈልጋት የመጣንበት መንገድ ያስረዳል ያሉት አቶ ግዛቸው በማዕከሉ ስልጠና የሚወስዱ የቀድሞ ታጣቂዎችም ወደየመጡበት አካባቢ ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ለህዝብና ለሀገር ልማትና ደህንነት ሲባል በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሰላምን መንገድ መከተል እንደሚጠበቅባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር የሕግ አማካሪ አቶ ታረቀኝ ታፈሰ፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የሳይኮ ሶሻል ስልጠና መደበኛና ሰላማዊ ህይወትን ለመምራት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የሰላም አማራጭን የተከተሉ አካላትን ሁሉ በማሰልጠን ወደ የመጡበት ማህበረሰብ የመቀላቀል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የተሀድሶ ስልጠና የቀድሞ ታጣቂዎች ከግጭት አስተሳሰብ ወጥተው በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዳባት ተሀድሶ ስልጠና ማዕከል ስልጠናቸውን የሚከታተሉ የቀድሞ ታጣቂዎችም ቀጣይ መደበኛ ህይወታቸውን የልማትና የሰላም አካል በማድረግ የበደሉትን ማህበረሰብ ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም የሰላም አማራጭን በመከተል ለወገናቸው ሰላምና ደኅንነት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡