የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለበርካታ ዓመታት ከመሩት ከ ኤ.ኤን.ሲ ፓርቲ አባልነት ተሰናበቱ

You are currently viewing የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለበርካታ ዓመታት ከመሩት ከ ኤ.ኤን.ሲ ፓርቲ አባልነት ተሰናበቱ
  • Post category:ዓለም

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ለበርካታ ዓመታት ከመሩት ከ ኤ.ኤን.ሲ ፓርቲ አባልነት ተሰናበቱ

AMN – ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም

እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ደቡብ አፍሪካን በፕሬዝዳንትነት የመሩትና በሙስና ቅሌት ከፕሬዝደንትነታቸው ለመልቀቅ የተገደዱት ጃኮብ ዙማ በአንድ ወቅት ይመሩት ከነበረውና ታሪካዊው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ( ኤ.ኤን.ሲ) ፓርቲ አባልነት መባረራቸው የበርካታ መገናኛ ብዙሃን የፊት ገጽ መረጃ ሆኗል፡፡

ባሳለፍነው ግንቦት ወር በተካሄደው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አዲስ የተመሰረተውን ኡምኮንቶ ዊስዝዌ (ኤም.ኬ)ን ፓርቲን ወክለው የምርጫ ዘመቻ ቢያካሄዱም የደቡብ አፍሪካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫው አንድ ሳምንት ሲቀረው ዙማን ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን የ15 ወራት እስራት ምክንያት በማድረግ በምርጫው በፓርላማ አባልነት እንዳይወዳደሩ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ ከ ኤ.ኤን.ሲ አባላት ጋር ቁርሾ ውስጥ አስገብቶ ጥርስ እንዲነከስባቸው አድርጓል፡፡

ከዚህ ሁነት በኋላ ፕሬዘዳንቱ በተደጋጋሚ የ ኤ.ኤን.ሲ አባል መሆናቸውን ሲናገሩ ቢቆዩም አፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ምክር ቤት አብላጫውን መቀመጫ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

የአንድነት መንግስት ለማቋቋም የተገደደው ኤ.ኤ.ን.ሲ የቀድሞውን መሪውን ከፓርቲው አባልነት ለመሰረዝ መገደዱን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስታውቋል።

እንደ ኤ.ኤ.ን.ሲ ዋና ፀሐፊ ፊኪሌ ምባሉላ ፓርቲው ለአመታት የነበረውን ተቀባይነትና ክብር ማጣቱ ዋናው ምክንያት ዙማ በመሆኑ ይህን ውሳኔ ሊተላለፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የ ኤ.ኤ.ን.ሲ ብሄራዊ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ባስተላለፈው በዚህ ውሳኔ ዙማ ከሌላ ፓርቲ ጋር በማበር እና የኤ.ኤ.ን.ሲ ፖሊሲዎች እንዲሁም አላማዎች በሚፃረር መልኩ በመንቀሳቀሳቸውና ታማኝነታቸውን በተግባር ባለማሳየታቸው ውሳኔው እንዲተላለፍ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ከመሩበት ፓርቲ መባረር ለብዙዎች አስደንጋጭ በመሆኑ ይህም ዳግም እንዲታይላቸው ግፊት እንደሚያደርጉ እየገለፁ የሚገኙት የኤም.ኬ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ውሳኔውም ዙማን ሳያሳትፍ የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን መሰል ክስ ያጣጣሉት የ ኤ.ኤ.ን.ሲ ፀሐፊው በውሳኔው ላይ ዙማ እንዲገኙ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ፍቃደኝነታቸው አለማሳየታቸውን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ፀሐፊ ፊኪሌ ምባሉላ ገለፃም በፓርቲው ውስጥ ህግን ጥሶ የተገኘን አካል በዲሲፕሊን የመጠየቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግለፅ በዙማም የተላለፈው ውሳኔ መነሻው ይህ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ዙማ በ1959 የኤ.ኤን.ሲ ወጣቶች ሊግን ተቀላቅለው የፓርቲ መሪ የሆኑ ሲሆን ኤ.ኤን.ሲ የ82 ዓመቱን ዙማን አባልነት በጥር ወር አግዶ እንደነበርም ይታወሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review