የቅድመ ወሊድ ዕረፍት ፋይዳ

ወይዘሮ ፀሐይ ይሁኔ በመንግስት ትምህርት ቤት ነው የሚሰሩት፡፡ እናትነት ፀጋ ነው፡፡ ይህ ፀጋ ደግሞ ከፅንስ እስከ ወልዶ ማሳደግ ድረስ ያለውን ጊዜ ያካትታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለእናቶችም ሆነ ለህፃናት ደህንነት ሲባል እናቶች እረፍት እንዲያደርጉ የተፈቀደውን የእናቶች የወሊድ ፈቃድ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡

ሦስት ልጆች እንዳሏቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ ሦስቱንም  ልጆቻቸውን ሲወልዱ የቅድመ ወሊድ ረፍት ወስደው አያውቁም፡፡ ለመስራትም እየተቸገሩ፣ እየደከማቸው ሁሉ ይሰሩ  እንደነበር አንስተው፤ ይህንንም የሚያደርጉት ከወሊድ በኋላ በቂ እረፍት አግኝተው ህጻኑን በአግባቡ ተንከባክበው ወደ ስራ ለመመለስ በሚል ነበር፡፡ አንዱን ወር ቀድመው ቢጠቀሙት የሦስት ወር ልጅ ትቶ ወደ ስራ መመለስ ከባድ መሆኑ ያሳስባቸው እንደነበርም ይናገራሉ፡፡

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ብርቱካን ዘለቀን ያገኘናቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በሰላም ተገላግለው ሁለተኛ ልጃቸውን  አቅፈው ነው፡፡ በአንድ የግል መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት ወይዘሮዋ፤ የወሊድ ፈቃድ  ጥቅም የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ብርቱካን ገለጻ፤ የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ ከወሊድ በኋላ (ድህረ ወሊድ) ይጠቅመኛል በማለት የቅድመ ወሊድ እረፍታቸውን እንዳልተጠቀሙ ያስታውሳሉ፡፡ ሁለተኛ ልጃቸውን ሲወልዱ ግን፣ እርግዝና ላይ እያሉ 36ኛ ሳምንታቸው ላይ የቅድመ ወሊድ ፈቃዳቸውን ተጠቅመዋል፡፡ በሚሰሩበት ካፌ ውስጥ ያለው የስራ ጫና በጣም ያስጨንቃቸውና ያደክማቸው ስለነበር፤ ረፍት በማድረጋቸው የተነሳ ጭንቀታቸው፣ ድካማቸው እንዲሁም በስራ መሰላቸታቸው ሁሉ ቀንሶላቸው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ይላሉ ወይዘሮዋ፤ ራሴን እንዳዳምጥ፣ ለመውለድ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንዳዘጋጅ እና ክትትሌን በአግባቡ እንዳደርግ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ መውሰዴ ጠቅሞኛል። ስለዚህ በተቻለ መጠን በተለይ ደግሞ እያመማቸው በኋላ ላይ ይጠቅመኛል በማለት የቅድመ ወሊድ እረፍታቸውን የማይጠቀሙ እናቶች እንዲጠቀሙ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ይመክራሉ።

ሚድዋይፍ አብነት በላይ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ለመንግስት ሰራተኞች የሚሰጠውን የወሊድ ፈቃድ አስመልክቶ በሰጡን ማብራሪያ እንደገለፁት፤ የእናቶች የወሊድ ፈቃድ ወይም እረፍት ሲባል ከመውለድ አንድ ወር በፊት እና ከወለዱ በኋላ ሦስት ወራት ወይም 90 ቀናትን በአጠቃላይ የ120 ቀናትን ያጠቃልላል፡፡

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ኃላፊ ሚድዋይፍ አብነት በላይ

90 ቀን የነበረው የእናቶች የወሊድ እረፍት ከታህሳስ 6 ቀን  2010 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 በአንቀፅ 42 ላይ ፈቃዱ ወደ 120 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው የራሱ አላማና ጠቀሜታ ስላለው ነው ይላሉ፡፡

የቅድመ ወሊድ እረፍት እናቶች ለመውለድ አንድ ወር ወይም 30 ቀናት ሲቀራቸው የሚወጡት ነው የሚሉት ሚድዋይፍ አብነት፤ ያለውንም ጥቅም ሲገልፁ አንደኛውና የመጀመሪያው በስራ ውጥረት ምክንያት የሚኖረውን የእግር ማበጥ፣ የወገብ ህመም እና የሰውነት መድከም በአጠቃላይ አካላዊ ህመምን ለማስታገስ እና ራስን ለመንከባከብ ይረዳል፡፡ ሌላኛው ጥቅም ደግሞ ከእርግዝናው ጋር ተዳምሮ በሚኖረው የስራ ጫና ምክንያት የሚኖረውን ጭንቀት ይቀንሳል።

የልጆችን የማህፀን ውስጥ እድገት ለማፋጠንና ለማመቻቸትም አስተዋፅኦው የጎላ ነው። አንዲት ረፍት ያገኘች እናት የመመገቢያ ጊዜ እንዲኖራት ስለሚያደርግ ጤነኛና እድገቱ የተስተካከለ ልጅ እንድትወልድም ያደርጋል፡፡

የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ጥቅሙ ይህ ብቻ አይደለም የሚሉት ሚድዋይፍ አብነት፤ ለወሊድ የመዘጋጃ ጊዜ ማለትም በሥነ ልቦና፣ በገንዘብ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማሟላት እድል የሚፈጥር መሆኑንም ነግረውናል፡፡

የአንዲት እናት አማካኝ የመውለጃ ጊዜ 40 ሳምንታት ነው የሚሉት ሚድዋይፍ አብነት፤ የቅድመ ወሊድ እረፍት የሚሰጠውም ከ36ኛ ሳምንት ጀምሮ ነው፡፡ የቅድመ ወሊድ እረፍት ማድረግ ጥቅም ሲኖረው ረፍት አለማድረግ ደግሞ እንዲሁ ጉዳትም አለው፤ ይህም ምጥ ያለ ጊዜው እንዲመጣ በማድረግ ልጆች ያለ ወቅታቸው እንዲወለዱ ያደርጋል፡፡ ወቅቱ ሳይደርስ የተወለዱ ልጆች ደግሞ የማደግ እድላቸውን ዝቅተኛ ያደርገዋል። ውጥረትና ጭንቀትን ያባብሳል፡፡ ለመውለድ ዝግጁ እንዳይሆኑም ያደርጋል ብለዋል፡፡  

እንደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልም ሰራተኞች ይሁኑ ተገልጋይ እናቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የቅድመ ወሊድ ፈቃዳቸውን ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን የቅድመ ወሊድ ፈቃድን ወደ ድህረ ወሊድ በመውሰድ የሚጠቀሙ እናቶችም ይበዛሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ለልጆቻቸው ጡት የሚያጠቡበት ጊዜ አጭር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አቶ መላኩ ተመስገን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሰው ሃብት ስራ አመራር ክትትል ድጋፍ ኦዲት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የእናቶችን የወሊድ ፈቃድ አስመልክቶ አዋጁንና አተገባበሩን እያጣቀሱ በሰጡን ማብራሪያ፤ የወሊድ ፈቃድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ 56/2010 ውስጥ ከተካተቱ የፍቃድ አይነቶች አንዱ ነው፡፡ 

የወሊድ ፈቃድ በአዋጁ አንቀፅ 42 ስር እንደተደነገገው ነፍሰጡር የሆነች ሴት መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ካሰበችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ እንዲሁም ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት በአጠቃላይ 120 ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፍቃድ ይሰጣታል። የወሊድ ፈቃድ የሚሰጥበት ዋነኛው አላማ የእናቶችን እና የህፃናቱን ደህንነት መጠበቅን ያለመ ነው፡፡

በዋናነት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ያስፈለገበት ምክንያት አንዲት እናት አመጋገቧን፣ ጤንነቷን እንዲሁም ህክምናዋን እንድትከታተል፣ በወሊድ ጊዜ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ እንዲቻል ተብሎ ነው። ነገር ግን የመንግስት ሰራተኛ ሴቶች ይህንን የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ወደ ድህረ ወሊድ በመውሰድ ልጆቻችንን “እንድንከባከብበት” ያግዘናል በማለት አይጠቀሙትም፡፡

እናቶች የቅድመ ወሊድ ፈቃዳቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ላሉ የሰው ሃብት አስተዳደር ክፍሎች ስልጠና ይሰጣል፡፡ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ይሰራል። እነሱ ደግሞ ለሰራተኞቻቸው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ

ያለውን ጠቀሜታ ግንዛቤ መፍጠርና  መከታተል አለባቸው። እኛም ባገኘነው አጋጣሚ እናቶች የቅድመ ወሊድ ፈቃድን እንዲጠቀሙ ነው የምንመክረው። ከባድና ጭንቀት ያለባቸው ስራዎች የሚሰሩ ሴቶች አሉ። የቅድመ ወሊድ ፈቃድ አለመጠቀም ለእነዚህ ሴቶች አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ይላሉ፡፡

በጥቅሉ እናቶች ከሚሰጣቸው የወሊድ ፈቃድ ውስጥ የቅድመ ወሊዱን እንደማይጠቀሙበትና ወደ ድህረ ወሊድ በማሻጋገር እንደሚወስዱ መረዳት ይቻላል፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም እንዳስረዱት የቅድመ ወሊድ እረፍት አለመጠቀም የራሱ የሆኑ የጤና እክሎችን ስለሚያስከትል፣ እናቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ግንዛቤ መፍጠር ይገባል እንላለን፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review