AMN – መስከረም 14/2017 ዓ.ም
ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በታላቅ ርብርብ እና ቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን ተላብሶ በውጤታማነት እንዲሠራ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት 12 ቀናት በአዳማ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ የሥልጠና መድረክ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ ተጠናቋል።
ፓርቲው “የሕልም ጉልበት ለእመርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ2000 በላይ ከፍተኛ የአመራር አባላቱ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ብልፅግና በማረጋገጥ የትውልዱን መፃኢ ዕድል ምቹና ስኬታማ ማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ሀሳቦች ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአመራር አባላቱ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የህዝብ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት በተግባር አንድነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በሥልጠናው በቂ አቅም ያገኙበትና የነገዋን ኢትዮጵያ መስራት የሚያስችል ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበረ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ሥልጠናው ሀገር ቀያሪም፣ ሀብት ፈጣሪም ሰው በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከተሞችና የፌዴራል ተቋማት ያለው ከፍተኛ አመራር በተመሳሳይ የፓርቲው ተልዕኮዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤት እንደሚያተጋው አብራርተዋል።
መሪነት ራስን መስጠትን፣ ሆደሰፊነትንና ዓላማን የማሳካት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ ከፍተኛ አመራሩ የወሰደው ሥልጠናም የመሪነት ቁልፍ መርሆዎችና ባህሪያትን በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ በመሆኑ ፈጣንና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ አቅም ይፈጠራል ሲሉ ገልጸዋል።
በሥልጠናው ሕልምንና ትልምን ለማሳካት የሚያግዙ እይታዎችና የመፈፀሚያ ትርክቶች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች፣ በህዝብ ቅቡልነትና ትብብር የመስራት አቅም፣ እውቀት መር ሽግግርን ለማፅናት የሚያስፈልጉ ሰብዕናዎች ላይ የመስራትና የፀጥታ ችግሮችን ወደ ተሟላ ሰላም የሚያሻግሩ ሂደቶችና የአመራር ስነምግባርን በሚመለከቱና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት መካሄዱን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።