የበልግ ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቆመ

You are currently viewing የበልግ ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቆመ

AMN- ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም

የበልግ ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ ተግባራትን ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

ዓለም አቀፍ የወባ ቀን “አዳዲስ ፈጠራዎችንና ሀብትን በማቀናጀት በሁሉን አቀፍ ቁርጠኝነት ወባን እንግታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዚያ 16 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከበር ተጠቅሷል።

አሁናዊ የወባ ስርጭትን በማስመልከት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው፣ ባለፉት ወራት በተሰሩ ስራዎች የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ባለፉት 8 ወራት ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ምርመራ በማድረግ የወባ በሽታ የተገኘባቸው የህክምና ድጋፍና ክትትል እንደተደረገላቸው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ ስርጭት የሚስተዋልባቸው 202 ወረዳዎች ላይ ክትትል መደረጉንና የስርጭት መጠኑን ከግማሽ በላይ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

ውጤቱ የተገኘው ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ስራ መሆኑንም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የወባ ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከመርሃ ግብሮቹ መካከል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር ሳይንሳዊ ኮንፍረንስ እና ሲምፖዚየም ከሚያዚያ 16 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በጅማ ከተማ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ለወባ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ህብረተሰቡ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና አካባቢን በማጽዳት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review