ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የትውስታ ማህደራቸው ላይ ግዙፍ ቦታ የያዘ ታላቅ በዓል ነው፡፡ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው ቢሆንም፣ ጥምቀትን ተከትሎ የሚከወኑ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ድምቀቱን ከፍ እንዲል አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያ ብዝሃ-ባህል ያላት ሃገር መሆኗን በሚገልጽ አኳኋን እንደየአካባቢው ወግና ልማድ ሃይማኖታዊ ዳራውን ሳይለቅ በዓሉ ውብ በሆነ መንገድ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን ባጋሩት አስተያየት፣ በኢትዮጵያውያን ትውስታ ጥምቀት ሰፊ ቦታ እንዲይዝ ካደረጉ ጉዳዮች መካከል ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ የአደባባይ ክዋኔዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የወል ክዋኔዎች ደግሞ የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከርና የባህል መወራረስ በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ በጥምቀት በዓል ጎልተው ከሚታዩ የወል ክዋኔዎች መካከል፣ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…” በሚል ለልጆች አዲስ ልብስ ተገዝቶላቸው በአደባባይ አምረው ይታያሉ፡፡ በዓለ- ጥምቀቱ በሚከበርበት ስፍራ ላይ ወጣቶች እና ልጆች እንደየዕድሜ እርከናቸው በነፃነት ይጨፍራሉ፡፡ ወጣቶች እግረ መንገዳቸውን ውሃ አጣጫቸውን ያስሳሉ። ዓይናቸው ባረፈባት ኮረዳ ላይም ሎሚ ይወረውራሉ፡፡ እነዚህንና ሌሎች የበዓሉ ክዋኔዎች በኢትዮጵያውያን መካከል የእርስ በእርስ ትስስር እንዲዳብር ትልቅ ሚና አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የጥምቀት አከባበር ለጎልማሶችና አዛውንቶች ታላቅ ትዝታ የያዘ ቢሆንም፤ ለህጻናትና ለወጣቶች ደግሞ ዛሬ ላይ እየተደሰቱ የሚኖሩት እጅግ ተናፋቂ በዓል ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል፤ እጅግ አዳዲስ ትዕይንቶችንና ክዋኔዎችን በማከል የጥምቀት በዓል አከባበር ዛሬም ድረስ እምር ብሎ በአደባባይ መከበሩን የቀጠለው፡፡ በተለይ መዲናችን አዲስ አበባ ጎዳናዎቿ ሰፍተው፣ መንገዶቿ ተውበውና አረንጓዴ ለብሰው ባማሩበት በዚህ ወቅት ጥምቀት መከበሩ ልዩ ድባብ እንዳለው አያጠራጥርም፡፡

አሁን ላይ በለውጥ ሂደት ላይ ያለችው አዲስ አበባ፣ ከዚህ ቀደም ጎዳናዎቿ ጠርዝ አልነበራቸውም፡፡ በጎዳናዎቿ ላይ የዓይን ማረፊያ የሚሆኑ ስፍራዎችን ፈልጎ ማግኘት ብርቅ ነበር፡፡ የእግረኛ መንገዶች አይደለም ለመንሸራሸር የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለመከወን እንኳን ብዙም የሚመቹ አልነበሩም፡፡ እነዚህና ሌሎች የአዲስ አበባ እንከኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ መሻሻሎች እያሳዩ ናቸው፡፡
አዎን! አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልከ-ብዙ ውብ ገጽታዎችን እየተላበሰች ነው፡፡ ጎዳናዎቿ ሰፍተዋል። አደባባዮቿ በአዲስ ገጽታ ተከስተዋል። በውብ መብራቶች የተሽቆጠቆጡት የከተማዋ መንገዶች በውበት ላይ ውበት አክለዋል፡፡ አረንጓዴ ለብሰውና በፋውንቴኖች ውበት ታጅበው እየፈኩ ናቸው፡፡ እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በዓላት በእንደዚህ አይነት ውብ የአደባባይ ድባብ መከበራቸው ለሃገር ገጽታ ብቻ ሳይሆን በዓሉ ቱሪስቶችን ይበልጥ እንዲስብ በማድረግ ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ወሰን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አቶ ሺመልስ ፀጋዬ ተወልደው ያደጉት እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ በተለምዶ ልደታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የጥምቀት በዓልን ከልጅነታቸው ጀምሮ እጅግ የሚወዱትና በፍቅር የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡ በዓሉን ለዓመታት በማኀደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አክብረዋል፡፡ በማግስቱ ጥር አስራ ሁለት የሚከበረውን ደግሞ በጎላ ሚካኤል በመገኘት ይታደሙ ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ከባለቤታቸውና ከሴት ልጃቸው ጋር በመሆን በጃን ሜዳ ነው የሚያከብሩት፡፡ አሁን ከቤተሰባቸው ጋር ተከራይተው የሚኖሩት ጃንሜዳ አካባቢ በመሆኑ ጥምቀትን በልዩ ድባብ የሚያከብሩባት ስፍራ ሆኗል፡፡ የተለያዩ ታቦታት ጃን ሜዳን ማደሪያቸው ስለሚያደርጉ የምዕመኑ ቁጥርም በዚያው ልክ ከፍተኛ እንዲሆንና ይኸም የበዓሉን ድባብ አስደሳች እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡
“ያለፉት አራት ዓመታት ከባለቤቴ ጋር በመሆን ጥምቀትን በጃን ሜዳ አክብሬያለሁ፡፡ በዓሉን ሳከበር ልጅነቴ ነው የሚታወሰኝ፡፡ የአርሞኒካ ጨዋታ፣ የተለያዩ ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደ ባህላቸው ለብሰውና እንደየቋንቋቸው ሲዘምሩ ሳይ እጅግ የተለየ ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡ አሁን ላይም ቢሆን ጥምቀት የአከባበር ድባቡ ይበልጥ እያማረ ቀጥሏል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ እየተሰሩ ያሉ ያማረ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫዎቱ ናቸው፡፡ በተለይ በርካታ ሰዎች የጥምቀት ዋዜማና የበዓሉ ዕለት ወደ ጎዳና ወጥተው ስለሚያከብሩ ምዕመኑ ከመኪና ጋር እየተጋፋ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ አሁን ላይ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ነው” ብለዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ያጋራን ወጣት ብሩክ ሃይሌ ነው፡፡ አውቶብስ ተራ በተለምዶ ኳስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ወጣት ብሩክ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የጥምቀት በዓል የሚያከብርበት ትዕይንት በህይወቱ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከሚይዙ ኩነቶች መካከል ቀዳሚው ነው ይላል፡፡
ጥምቀት በዋናነት ሃይማኖታዊ መልክ ቢኖረውም በዓሉን አስታከን የምናደርጋቸው ክዋኔዎችና የምናያቸው ትዕይንቶች እጅግ አስደሳች ናቸው ይላል፤ ወጣት ብሩክ፡፡ “እኔ ባደግኩበት ኳስ ሜዳ ያለው የአዲሱ ሚካኤል (የቅዱስ ሚካኤል) ታቦት ስለሆነ፣ ጥምቀት ከከተራው ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ ለሶስት ቀናት ነው የሚከበረው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን አጠቃላይ በአካባቢው ከከተራ አንስቶ እስከ ቃና ዘገሊላ ድረስ ያሉ ቀናት እንደ ብሔራዊ በዓላት ነው የሚያከበሩት፡፡ እኔም ልጅ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን አዲስ ልብስ ለብሰን በየቦታው ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ዝክሮች ወይም ድግሶች ዞረን ስንበላ የምንውለው ነገር ዛሬም ድረስ የምናፍቀው ትዕይንት ነው” ሲል አጫውቶናል፡፡
ወጣት ብሩክ ለዓመታት የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓል ሲያከበር የቅዱስ ሚካኤል ታቦት በፓስተርና በጳውሎስ ሆስፒታል አድርጎ ወደ ማደሪያው አበበ ቢቂላ ስቴድየም አካባቢ ሲጓዝና ሲመለስ መንገዶች በጣም ስለሚጨናነቁ ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህን ችግር የሚፈታ ስራ እንደተሰራ አጫውቶናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በተለይ ከፓስተር ወደ መድኃኒዓለም የሚወስደው የእግረኛ መንገድ ሰፍቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ጥምቀትን ይበልጥ እንዲደምቅና የቱሪስቶች ቀልብ እንዲስብ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ወጣት ብሩክ አብራርቷል፡፡
እንደ ወሰን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የሕዝቦችን አንድነት በማጠናከርና ባህልን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሻገር ረገድ ብዙ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበር በአደባባይ የሚከበር በዓል ስለሆነ የውጭ ሃገር ሰዎች ወይም ቱሪስቶች መጥተው ከህብረተሰቡ ጋር አብረው ለማክበር የሚያስችላቸው ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ድባቡን ከፍ ለማድረግ ምቹ ስፍራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ጎዳናዎችን የማስፋት፣ ነጻ ስፍራዎችንና የአይን ማረፊያ አካባቢዎችን ምቹ እና ውብ ከማድረግ አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በዓሉ ይበልጥ እንዲጎላ ያደርጉታል፡፡ በተለይ የበዓሉ አከባበር ላይ ቱሪስቶችን ለመሳብ አሁን ካለው ይበልጥ ታቅዶና ታስቦ መሰራት አለበት። ጥምቀት በአደባባይ ሲከበር ለማየት የሚመጡ ከውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎችን ይበልጥ መሰራት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያም ከጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ፋይዳው ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘት አለባት ብለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥኑ ፕሮጀክቶች ባለቤት እየሆነች ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የውጭ ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆን በሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ጭምር እየተወደዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ቱሪስቶች በዋናነት ወደ ሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመሸጋገር ገብተው የሚውጡባት ከተማ እንደነበረች የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ዝንባሌ የሚቀይሩ ተግባራት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በስፋት በመሰራታቸው አዲስ አበባ የምታስጎበኛቸው ተፈጥሯዊ መስህቦችና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በዓላት ይበልጥ ጎልተው እንዲታዩና ቱሪስቶችም ወደ ሃገር መጥተው የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑ እነዚህ የመዲናዋ ፕሮጀክቶች ጥሩ መደላድል ይፈጥራሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ