የበዓል አመጋገብ እና ጤና

የበዓል አመጋገብ እና ጤና

በበዓላት ወቅት ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጓደኛና፣ ጎረቤት በመሰባሰብ ቤት ያፈራውን ምግብና መጠጥ በጋራ መብላትና መጠጣት የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት እሴታቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በበዓላት ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ የተለያዩ የምግብና የመጠጥ ዓይነቶችን መመገብ የተለመደ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በበዓላት ወቅት በሚከናወን አመጋገብ ምክንያት ጤናቸው ሲታወክ ይስተዋላል።

ይህም አንዳንዴ ላልተጠበቀ ህመም አለፍ ሲልም ለሕይወት ማለፍ ሊዳርግ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በመሆኑም በዓልን በሰላም ለማክበር ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል የበዓላት ሰሞን አመጋገብ አንዱና ዋነኛው ሲሆን፣ ጤናማ የበዓል አመጋገብን በመከተል ጤናን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በበዓል ወቅት የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ማለትም እንደ ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦችን መመገብ የተለመደ ሲሆን በተለይም በፆም ምክንያት ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየ ጨጓራ በአንድ ጊዜ እነዚህን የቅባት ምግቦች ለመቀበል ይቸገርና ለሕመም የሚዳርግበት አጋጣሚ እንደሚኖር ነው የሚገለጸው፡፡

እነዚህ ምግቦች በተፈጥሯቸው ከፍተኛ ቅባት ያላቸው በመሆናቸው በጨጓራችን ውስጥ ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መሰል ሕመሞችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የስነ ምግብ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡

ሰዎች በበዓል ወቅት አልኮልን የምግብ መፈጨትን ያፋጥናል በማለት እና እንደ መዝናኛ በመቁጠር በብዛት ይጠቀማሉ። ነገር ግን አልኮልን አብዝቶ መውሰድ ጉበትን ለጉዳት የሚዳርግ በመሆኑ በበዓል ሰሞን ስጋን እና አልኮልን በአንድ ላይ መውሰድ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ጥናቶች ያሳያሉ።

የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በበዓላት ወቅት ሰዎች ከአመጋገብ ጋር በተገናኘ የተለያየ የጤና እክል እንደሚገጥማቸው ገልጾ፣ የበዓላት ወቅት ጤናማ አመጋገቦችን መከተል እንደሚገባ ይመክራል፡፡

ሰዎች በበዓላት ወቅት ጣፋጭ ምግቦችን ከተመገቡ በኋላ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ በተለይም በእግር መሄድ ከሚከሰት የጤና መታወክ ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉ ማዕከሉ ያብራራል።

በበዓል ወቅት ሰዎች ጨው፣ ጮማና የስኳር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ የምግብ አይነቶችን አብዝቶ ከመጠቀም መጠንቀቅ እንደሚገባም ይመክራሉ ባለሙያዎቹ፡፡

በበዓል ወቅት በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ እንደ ተልባና ሱፍ ያሉ ምግቦችን ቀድሞ በመመገብ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የሥርዓተ ልመት አካሎች ወደ መደበኛው ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ሌላኛው ተገቢ መፍትሔ መሆኑንም የስነ ምግብ ባለሙያዊች ያስገነዝባሉ፡፡

በተጨማሪ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገም ተግባራዊ ማድረግ ጤናን ለመጠበቅ እንደሚያስችል የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል መረጃ ያመላክታል፡፡

AMN – ታኀሣሥ 29/2017 ዓ.ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review