የበዓል ደስታ ነጣቂው አደጋ

“የቀን ጎዶሎን ሚዳቋም አትዘለውም” ብለው ባለታሪካችን ታሪካቸውን ጀመሩልን። “የበዓል ዋዜማ ነበር በግ ለመግዛት ወደ ገበያ የወጣሁት። ገበያው ደርቷል፤ ግብይቱም ተጧጡፏል፤ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ለመሸመት ከቦታ ቦታ ይዟዟራሉ፤ እኔም ከገበያተኛው አንዱ ነበርኩ። በጉን ገዝቼ በጉጉት ወደሚጠብቁኝ ቤተሰቦቼ ለመድረስ ከእግረኛ መንገድ ውጭ አስፓልት ሳቋርጥ ነበር የመኪና አደጋው የተከሰተው” ይላሉ የ60 ዓመት አዛውንቱ አቶ አስራት አለሙ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ)፡፡

“አደጋው የደረሰብኝ ስድስት ኪሎ አካባቢ ሲሆን፤ በግ ይዞ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ቤተሰቦቼ በድንገት ወደ አቤት ሆስፒታል መግባቴ ተነገራቸው፡፡ በወቅቱ ራሴን ስቼ ስለነበር የማውቀው ነገር አልነበረም፤ ለቤተሰቦቼ ግን አስደንጋጭና መሪር ነበር፡፡

በደረሰብኝ የትራፊክ አደጋ አንድ እግሬ ተሰብሯል፡፡ በወቅቱ ራሴን ሳውቅ የደረሰብኝን የአካል ጉዳት አምኜ ለመቀበል ተቸገርኩ፡፡ በእንዲህ አይነት አጋጣሚ አካል ጉዳተኛ መሆኔ ውስጤን ጎዳው፡፡ በሃሴትና በደስታ ልናሳልፈው ያሰብነውንም በዓል በሆስፒታል ውስጥ በለቅሶ አሳለፍነው” ሲሉ ያን ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡

አቶ አስራት የሚራመዱት በቀኝ በኩል የአካል ድጋፍ (ክራንች)  በመጠቀም  እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ቆፍጣና ነበርኩ ዛሬ እንዲህ ሆንኩ፤ የቤት እመቤት የሆነችው ባለቤቴም ገንዘብ በማጣት እኔንና ልጆቻችንን የምትመግበን ስታጣ እንባ ይቀድማታል” ሲሉ የመኪና አደጋ ጉዳቱ የት ድረስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡    

የበዓል ሰሞን ከምንሰማቸው ዜናዎች መካከል የትራፊክ አደጋ አንዱ ነው፡፡ ለደስታ እና ለጨዋታ ሲባል ሰብሰብ ብሎ የመጠጣት ብሎም መኪና ማሽከርከር ከምክንያቶቹ መካከል አንዱ ነው፡፡

ኢንስፔክተር ታምሩ ደግፈው በአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የህዝብ ግንዛቤ ማስተባበሪያ ሃላፊ ናቸው። በቅርብ ጊዜ ወደ ሃላፊነቱ ቦታ ይምጡ እንጂ የትራፊክ እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ በማድረጉ ረገድ 25 ዓመታትን አገልግለዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የአልኮል የትንፋሽ ልኬት ሲደረግ

ኢንስፔክተሩ እንደተናገሩት፣ በበዓላት መቃረቢያ በተለይ አዲስ ዓመትን ለየት የሚያደርገው ከክረምት መውጣትና ዘመድ ለዘመድ መጠያየቅ ጋር ተያይዞ ሰዎች ከሃገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ሃገራት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ ለሸመታ የሚደረገውም እንቅስቃሴ የትራፊክ ፍሰቱ እንዲጨምርና አደጋውም በዚያው ልክ እንዲከሰት ያደርገዋል፡፡

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ፣ በበዓላት ሰሞን ለሚከሰት የትራፊክ አደጋ እንደ ምክንያት የሚቀመጠው ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ቅድሚያ ለሚገባው ተሽከርካሪ እና እግረኛ ቅድሚያ አለመስጠትና የእግረኞች የጥንቃቄ ጉድለት ተጠቃሽ ነው፡፡ በረጅም ዓመታት ቆይታቸውም አንዳንድ የማይጠበቁ ዓይነት የተሽከርካሪ አደጋዎች ሲከሰቱ አጋጥሟቸዋል፡፡ “አደጋዎቹን ማየት በጣም ይረብሻል፡፡ ከአደጋው ቦታ የምናነሳቸው ሰዎች መጠንቀቅ ሲችሉ ለዚያ መሰል አደጋ መዳረጋቸው ያሳዝናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አደጋ ሲደርስ ኃላፊነታችንን እንዳልተወጣን ይሰማናል፡፡ ስራችንን እንደሰራን የሚሰማን ሰው በሰላም ወጥቶ ሲገባ ነው” ይላሉ፡፡ 

አደጋዎችን ለመከላከልም፣ “ታምሞ ከመማቀቅ” እንዲሉ በሰራተኛ መግቢያና መውጫ ሰዓት፣ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች እንዲሁም ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ትኩረት አድርገን ነው የምንሰራው፡፡ በአደባባዮች ከትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ጋር በመሆን በአሽከርካሪዎች ላይ የአልኮል የትንፋሽ ልኬት ይደረጋል፡፡ አንድ አሽከርካሪ ከተፈቀደው የአልኮል መጠጥ መጠን በላይ ተጠቅሞ ከተገኘ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ተሽከርካሪውን በማስቆም ቤተሰብ እንዲወስደው ይደረጋል፡፡ ተሽከርካሪውን የሚወስድ ከሌለ ደግሞ አሽከርካሪውን በሌላ መኪና በመላክ ተሽከርካሪው እንዲቆም በማድረግ  እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ይህ አንዱና ጠጥቶ ማሽከርከር የሚያስከትለውን አደጋ የምንቀንስበት ነው ይላሉ፡፡

ከውጭ ሃገር የሚመጡ እግረኞችም ይሁኑ አሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በርካታ መሰረተ ልማት የተሰሩባትን አዲስ አበባ አማራጭ መንገዶች፣ የተለያዩ ማመላከቻዎች ላይ ግንዛቤው ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱ እየተሰራ ነው፡፡

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለፃ፤ በበዓላት ወቅት ተልዕኳቸው እንደ ትራፊክ ፖሊስ ብቻ ሳይሆን ወንጀልን ለመከላከል ተልዕኮ ወስዶ እንደወጣ የአንድ ተቋም ባለሙያ ነው። ትኩረታቸውም በቅድመ አደጋ እና በቅድመ ወንጀል መከላከል ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው። ሰዎች የተለያዩ የበዓል  ግብይቶችን ለመፈፀም ወደ ገበያ ቦታዎች ይወጣሉ። እነዚህን አካላት በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡና በዓላቱንም ተደስተው ሲያሳልፉ መመልከት ለእሳቸው በበዓሉ ከሚደሰቱት  በላይ የመንፈስ እርካታን እንደሚያስገኝላቸው ይናገራሉ፡፡

በበዓላት  ሰሞን (ዋዜማ፣ እለት እና ከበዓል በኋላ) ባሉት ቀናት የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ከወትሮው ለየት የሚያደርገው የመጀመሪያው፣ ጠጥቶ ማሽከርከር ሲሆን፤ ሰዎች ለበዓሉ ዝግጅት መውጣታቸው፣ ተሽከርካሪዎችም እቃዎችን ይዘው ወደ ከተማ መግባታቸው እና እንቅስቃሴዎች መኖራቸው እንደሆነ የነገሩን ደግሞ የአውቶ ሴፍቲ የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅና የመንገድ ደህንነት ባለሙያው ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ናቸው፡፡ 

“አልኮል የጠጣ  ሰው የማገናዘብ፣ የማየት እና ውሳኔ የመስጠት አቅሙን በማዳከም በደመነፍስ እንዲያሽከረክር ያደርገዋል፡፡ ይህ ሲሆን አደባባይ ላይ መውጣት፣ አስፓልቱን በመሳት ከግኡዝ ነገሮች ጋር የመጋጨት እንዲሁም መኪና የመገልበጥ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ለቁሳዊ  እና አካላዊ ጉዳት ያጋልጣል” ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢንስፔክተር አሰፋ በበዓላት ሰሞን ካጋጠሟቸው ገጠመኞች ውስጥ ሰዎች መኪናቸውን አቁመው ተዝናንተው ሲመለሱ መኪናቸውን የት እንዳቆሙት ዘንግተው ለፖሊስ ያመለከቱበትን አጋጣሚ ያስታውሱታል፡፡ በሌላ በኩል በሚሊኒየሙ 2000 ዓ.ም አንድ ወጣት አልኮል ጠጥቶ ቀበቶ ሳያስር ሲያሽከረክር መኪናው ተገልብጦ ህይወቱ ያለፈበትን፣ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ባልና ሚስት የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች እርስ በርስ ተጋጭተው የሞቱበት ቀን የማይዘነጓቸው አሳዛኝ ገጠመኞቻቸው መሆናቸውን ነግረውናል፡፡

አደጋው ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና የሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ “በከተማዋ በ2014 ዓ.ም 411 ሰዎች ላይ  የሞት፣ 1 ሺህ 900 ከባድ የአካል ጉዳት፣ 1 ሺህ 213 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 29 ሺህ 170 የንብረት ውድመት ያስከተሉ የትራፊክ አደጋዎች ተከስተዋል። በ2015 ዓ.ም 393 ሰዎች ላይ የሞት፣ 1 ሺህ 909 ከባድ የአካል ጉዳት፣ 1 ሺህ 486 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 32 ሺህ 992 የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 383 ሰዎች ላይ የሞት፣ 2 ሺህ 92 ከባድ የአካል ጉዳት፣ 1 ሺህ 573 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 34 ሺህ 47 የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡”

የመስከረም ወር አዲስ ዓመትና የተለያዩ በዓላት የሚከበሩበትና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበት በመሆኑ የትራፊክ ፍሰቱ ከፍተኛ በመሆኑ ለአደጋ መከሰት ምክንያት እንደሚሆን ኢንፔክተር ሰለሞን ያነሳሉ፡፡ በ2015 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 122 ሰዎች  ላይ የሞት፣ 499 ከባድ የአካል ጉዳት፣ 359 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 8 ሺህ 31 የንብረት ውድመት ያስከተሉ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ በተመሳሳይ በ2016 በጀት ዓመት 106 ሰዎች ላይ የሞት፣ 494 ከባድ የአካል ጉዳት፣ 385 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 8 ሺህ 253 የንብረት ውድመት ያስከተሉ አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የሞት አደጋ እና ከባድ የአካል ጉዳት መቀነስ አሳይቷል፡፡ ቀላል የአካል ጉዳት እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ደግሞ ጨምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡን ማብራሪያ፣ ጠጥቶ በማሽከርከር፣ መኪና ለሌላ ወገን አሳልፎ በመስጠት፣ ከመጠን በላይ መጫን፣ ከልክ በላይ በሆነ ፍጥነት በማሽከርከር የሚከሰቱ አደጋዎች በበዓላት ሰሞን ለሚከሰቱ የትራፊክ  አደጋዎች መንስኤ ናቸው፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ኤጀንሲው በዋናነት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም ህዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች በመለየት ለአሽከርካሪዎችና ለእግረኞች በአሥራ አንድ ክፍለ ከተሞች የገፅ ለገፅ ግንዛቤ ፈጠራ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሜ፣ ማክሰኞ እና ሐሙስ  የነበረውን የአልኮል ቁጥጥር በበዓላት ሰሞን በሁሉም ቀናት ልኬት እንዲደረግ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም ማለት በበዓላት ሰሞን ጠጥተው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን በትንፋሽ መለኪያ መሳሪያ ልኬት ማካሄድ ነው። በዚህም መሰረት በ2016 በጀት ዓመት ከ20 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ 16 ሺህ የሚሆኑት በመጠኑ የጠጡ እና 4 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ከመጠን በላይ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ የተገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ለ24 ሰዓት መንጃ ፈቃድ እንዲወሰድባቸውና ተሽከርካሪው እንዲቆም በማድረግ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረት የተቀመጠውን ክፍያ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡

ሌላኛው የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የምንጠቀምበት የፍጥነት መቀነሻዎችን በፕላስቲክም፣ በኮንክሪትም መስራት፣ ሄልሜት ሳይለብሱ የሞተር ብስክሌትን የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው። የተሰሩት የኮሪደር ልማቶች ለእግረኛም ሆነ ለአሽከርካሪ ምቹ መሆናቸውን ጨምሮ የሚደረጉት የቁጥጥር ስራዎች አደጋዎችን ለመቀነስ እንዳስቻላቸው ነው የነገሩን። ለዚህ በዋናነት አመራሩና አባሉ የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው አካባቢዎች 24 ሰዓታት የቁጥጥርና ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

“የትራፊክ አደጋ በቅፅበት የሚከሰት ነው” ያሉት  ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወቅቱ ክረምት እና መጭውም በዓል እንደመሆኑ መጠን ማህበረሰቡ የእግረኛ መንገዶችን በአግባቡ በመጠቀም፣ አሽከርካሪውም በጥንቃቄ በማሽከርከር የድርሻውን በመወጣት በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስቀረት እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ 

“አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የደስታ፣ የሃሴት፣ አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት የምናቅድበት ትልቅ ወር ነው” ያሉት ኢንስፔክተር አሰፋ በበኩላቸው፣ በበዓል ሰሞን በተቻለ መጠን እግረኛውም ይሁን አሽከርካሪው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መንቀሳቀስ አለበት። በትራንስፖርት ስራ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎችም የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሰው በማሽከርከር ራሳቸውንና እግረኛውን ከአደጋ መጠበቅ አለባቸው። ማህበረሰቡም ለደስታው ገደብ በማበጀት በተረጋጋ መንፈስ በዓሉን ማክበር እንደሚገባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ኢንስፔክተር ታምሩ በበኩላቸው፤ የትራፊክ አደጋው ከንብረትም ባለፈ የአካልና በህይወት ላይ የከፋ ጉዳት ስለሚያስከትል እግረኛውም ሆነ አሽከርካሪው ህግ አስከባሪ ኖረም አልኖረም የመንገድ አጠቃቀማቸውን ማስተካከል፣ ሲያሽከረክሩም መጠንቀቅ አለባቸው ብለዋል፡፡ “አዩኝ አላዩኝ” ብሎ የሚፈፅመው አግባብነት የሌለው ድርጊት መኖር የለበትም። መሰረተ ልማቶችም ከፍተኛ የሃገር ሃብት ፈስሶባቸው የተገነቡ በመሆናቸው ለእነዚህ የሃገር ሀብቶች ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 2023 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም ላይ በየዓመቱ 1 ነጥብ 19 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሳቢያ ይሞታሉ፡፡ በዚህ አደጋ ዋነኞቹ  ተጠቂዎች ከ5 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

መረጃው አክሎም፤ በዓለም ላይ ከሚደርሰው የሞት አደጋ 92 በመቶ የሚሆነው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ ነው፡፡ ከሚከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እግረኞች፣ ብስክሌተኞችና የሞተር ብስክሌተኞች እንደሚገኙበትም ይገልፃል፡፡

እኛም መጪው በዓል የሰላምና የደስታ እንዲሆን እየተመኘን፣ የትራፊክ አደጋን ጨምሮ ሕይወትን ከሚቀጥፉ ብሎም ከሚያመሳቅሉ ነገሮች ራስን መጠበቅ እና ተገቢውን ጥንቃቄም ማድረግ ይገባል እንላለን፡፡ 

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review