የበጎነት ፍሬ

You are currently viewing የበጎነት ፍሬ

“በንፁህ የመኖሪያ አካባቢ እየኖርን ነው”

በበጎ ፈቃድ ቤት የተገነባላቸው ወይዘሮ ሻሼ ሸኖ

በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ፣ እየጎለበተና እያበበ መጥቷል፡፡ በርካቶች በበጎ ፈቃደኝነት ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘባቸውን በመስጠት የወገናቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያቃለሉ ይገኛሉ፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊትም ተጠባቂው የ2017 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡ ከንቲባዋ በወቅቱ እንደተናገሩት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኝነት ተቋማዊ እንዲሆን ተደርጎ በመሰራቱ በርካታ የዘመሙ ጎጆዎች፣ ጠያቂ የሌላቸው እናቶች፣ አባቶች፣ የሀገር ባለውለታዎች ቀና እንዲሉ ያደረጉ፣ የሚሊዮኖችን እንባ ያበሱ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት የአንድ ወቅት ስራ ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ተግባር፣ በትውልዱ ዘንድ ባህል እንዲሆን መሰረት ተጥሏል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቀየራቸው የከተማዋ አካባቢዎች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከፓስተር አደባባይ ዝቅ ብሎ የሚገኘው “ገብስ ሜዳ” እየተባለ የሚጠራው አንዱ ነው፡፡ የተፋፈጉ፣ ከእንጨት፣ አፈርና ቆርቆሮ የተሰሩ፣ አንዳንድ ቦታ ፕላስቲክ የተወጠረባቸው፣ የጣሪያቸውን ቆርቆሮ ነፋስ እንዳይወስደው ከላይ ድንጋይ የተጫነባቸው …  መኖሪያ ቤቶች ያሉበት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዋናነት ቆሎ በመሸጥ የሚተዳደሩት ነዋሪዎቹ፣ ገብስ እየፈተጉና እየቆሉ ሲያዘጋጁ ከቤት እየተንቦለቦለ የሚወጣው ጭስ በራሳቸው ደህንነትና ጤና ላይ አደጋ የሚያስከትል እንደነበር ነዋሪዎቹ በአንደበታቸው ይመሰክራሉ፡፡ 

ወይዘሮ ሻሼ ሸኖ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በአካባቢው ኖረዋል፤ ወልደው፣ ልጅ አሳድገዋል፡፡ አራት ልጆችን ጨምሮ ስድስት የቤተሰብ አባላት አላቸው፡፡ ልክ እንደ አብዛኛው የሰፈሩ ነዋሪዎች ገብስ እየፈተጉ፣ ቆሎ ቆልተው እየሸጡ ነበር ኑሯቸውን ሲመሩ የቆዩት፡፡

ቤታቸው “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” እንደሚባለው አቅም ስለሌላቸው ችለው ኖሩበት እንጂ ብዙ ችግሮች ያሉበት እንደነበር ወይዘሮ ሻሼ አልሸሸጉም፡፡ “ቤታችን ቆሻሻ ነው፤  ከስራው ባህርይ አኳያ ልብሳችንም የቆሸሸ ነበር፤ አቧራ አለ፡፡ በአንድ መፀዳጃ ቤት እስከ ስድስት ቤተሰብ ነበር በጋራ የምንጠቀመው፡፡ ማዕድ ቤቱም ከቤት ውጭ ሆኖ ሁለት ምድጃ ተሰርቶ በርካታ ሰው እየተጋፋ በጋራ የሚጠቀምበት ነበር። በክረምት ወቅት ዝናብ ሲዘንብ የሚፈጠረው ጎርፍም በቤቱ አካባቢ ስለሚሄድ “አንድ ቀን’ ቤት ይገባል” በሚል ይሳቀቁ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ 

ሌላኛዋ የሰፈሩ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይነሽ ጫላ ይባላሉ፡፡ እሳቸውም በአስተያየታቸው ለበርካታ ዓመታት ይኖሩበት የነበረው መኖሪያ ቤት ለዘመናዊ አኗኗር የማይመች እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ “በፊት የነበረው የመፀዳጃ ቤት ሁኔታ የሚወራ ነገር አይደለም።” የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይነሽ፣ በአንድ ግቢ ውስጥ በርካታ ቤተሰብ በአንድ መፀዳጃ ቤት ወረፋ እየጠበቅን ነበር የምንጠቀመው፡፡ ማዕድ ቤትም ቢሆን በጋራ ነበር የምንጠቀመው፤ ከስራውም ባህርይ፣ ከቤቱ እርጅና ጋር ተያይዞ መኖሪያ ቤታችን የተጎሳቆለ ነበር። የእሳት አደጋም በተለያዩ ጊዜያት ያጋጥም እንደነበርና እሳቱን ለማጥፋትም የአደጋ መውጫና መግቢያ እንዳልነበር አንስተውልናል፡፡

በገብስ ሰፈር የነበሩ መኖሪያ ቤቶች ያረጁ፣ ንጽህና የጎደላቸው፣ ለዘመናዊ አኗኗር የማይመቹ እንደነበሩ እነ ወይዘሮ ሻሼ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የአካባቢው ማህበረሰብ ይመሰክራል። ነዋሪዎቹ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል በመሆኑ የዘመመውን ጎጇቸውን ለማቃናት አቅም አልነበራቸውም።  ለበርካታ ዓመታት ተዘንግተው የቆዩ፣ ያረጁና የተፋፈጉ መኖሪያ ቤቶች ሲኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች በከተማ አስተዳደሩና ልበ ቀና በጎ ፈቃደኞች ትብብር ፈርሶ፣ መንገድ፣ የህፃናት መጫዎቻና ማቆያ፣ ዘመናዊ የመጸዳጃና የማብሰያ ቦታዎች፣ እንዲሁም የጋራ መገልገያ ስፍራዎች ያካተቱ ዘመናዊ ህንፃዎች ተገንብተው ተላልፈዋል፡፡ ሰፈሩም በጎነት ቁጥር 3 የመኖሪያ መንደር ተብሏል፡፡

ደሳሳው ቤታቸው ፈርሶ፣ ውብና ዘመናዊ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ባሟላ መልኩ ተገንብቶ ተጠቃሚ በመሆናቸው ነዋሪዎች ደስተኞች ናቸው፡፡ ከነበሩበት ህይወት እንዲወጡ ቤቶችን በመገንባት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረገው የከተማ አስተዳደሩ ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባሉ። ወይዘሮ ሻሼ በዘመናዊው ባለአምስት ወለል የበጎነት ቁጥር 3 መንደር ላይ ባለአንድ መኝታ ቤት ተሰጥቷቸዋል። የራሳቸውን ማዕድ ቤት፣ መኝታ ቤት እና  መፀዳጃ ቤት አግኝተዋል፡፡ “አሁን ጤናችን ተጠብቆ፣ በንፁህ መኖሪያ አካባቢ እየኖርን ነው። አዲስ አበባን አሁን ነው ያየናት፤ በፊት ከተማ እየኖርን ነው እንላለን እንጂ ከገጠር አይሻልም ነበር። ከዚህ በኋላ ‘ተመስገን’ እያልን ነው የምንኖረው፡፡ ለዚህ እንድንበቃ ላደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡

አዲሱ ቤት ሲገነባ ሰባራ ሳንቲም ሳያወጡ በከተማ አስተዳደሩና በጎ ፈቃደኞች ትብብር እንደተሰራላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሀይነሽ፣ “ከአፈር ቤት ወጥቼ ጽዱና ሁሉንም አገልግሎት ያሟላ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው፤ ተመስገን ከማለት ውጪ የምለው የለኝም” ሲሉ ነው የተሰማቸውን የደስታ ስሜት በቃላት ለመግለፅ እንደሚቸገሩ የተናገሩት፡፡ 

በአዲስ አበባ ባለሀብቶችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተቋማትና የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ የሚሰራው የበጎነት ተግባር በቤት ግንባታና እድሳት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ መንገድ ላይ ዜጎች የትራፊክ አደጋ ሰለባ እንዳይሆኑ በማስተናበር፣ በሆስፒታሎች ህሙማንን በመርዳት፣ ማዕድ በማጋራት፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ በመትከልና በሌሎች መስኮች በርካታ ዜጎች በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍ የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በማቃለል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡

በመንገድ ትራፊክ ማስተናበር ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ ወጣቶች መካከል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሸጎሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት አበበ ጣሰው አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ በትራፊክ ማስተናበር ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሳተፍ ምክንያት የሆነው በአንድ ወቅት በሚኖርበት ሰፈር ዳቦ ከሱቅ ለመግዛት መንገድ ሲያቋርጥ የነበረ ወጣት በመኪና ተገጭቶ ጉዳት ሲደርስበት መመልከቱ ነበር፡፡ በወቅቱ ልጁ ህክምና እንዲያገኝ ከማገዝ ባሻገር “በአካባቢው መንገድ ላይ የሚያስተናብር ቢኖር አደጋ አይደርስም ነበር” በሚል ቁጭት ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፍ እንደጀመረ ይናገራል፡፡ 

ላለፉት ሰባት ዓመታትም በመንገድ ትራፊክ ማስተናበር እያገለገለ ይገኛል። የግል ስራውን በጠዋቱ ካከናወነ በኋላ ከቀኑ ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ፤ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በቋሚነት ይሰራል፡፡

“ስራው የሰውን ነፍስ ማዳን ነው። በበጎ ፈቃድ በመሳተፌ ትልቅ እርካታ ነው የማገኘው፡፡ ከስራው ስቀር ደስታ ይርቀኛል፤ በጎ ፈቃደኝነት ሱስ ነው።” ሲልም በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፉ ስለሚፈጥርለት ስሜት ይናገራል። አንዳንዶች የገንዘብ ድጋፍና ጥቅም አግኝተን የምንሰራ  ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን አረጋውያን፣ አይነ ስውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህፃናት ያለ ስጋት ከትራፊክ አደጋ ተጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ በነፃ ነው የምናገለግለው፡፡ ህብረተሰቡ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አደራ ጥሎብናል፡፡ በምንሰጠው አገልግሎትም ደስተኛ ነው፤ ያበረታታናልም ይላል ወጣት አበበ፡፡

ወጣት አበበ በጉለሌ ክፍለ ከተማ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት አካባቢ በሚገኘው መንገድ ላይ ነው የትራፊክ ማስተናበር ስራውን የሚያከናውነው፡፡ አካባቢው ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማትና የተለያዩ የንግድ ስራዎች ያሉበት፣ ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት ነው፡፡

በጎ ፈቃድ የሰዎችን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ራሳችንንም ሆነ ቤተሰባችንን የመንገድ አጠቃቀም ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ከትራፊክ አደጋ እንዲጠበቁ ለማድረግ ያስችላል፡፡ በሀገራችን ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ከሆኑት መካከል የትራፊክ አደጋ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ሁሉም ሰው በየአካባቢው፣ በሰፈሩ መኪና እና ተሽከርካሪ ባለበት አካባቢ ሁሉ የራሱን እገዛ ቢያደርግ የብዙ ሰው ህይወት ማትረፍ እንደሚቻልም ወጣቱ ያስገነዝባል፡፡

የመንገድ ትራፊክ አስተናባሪ በጎ ፈቃደኞች ህብረተሰቡ በተለይ ህፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ መንገዶችን እንዲሻገሩ በማስቻል እያደረጉት ያለው ድጋፍ ቀላል ዋጋ ያለው እንዳልሆነ የአካባቢው ነዋሪ አቶ አዲሱ ተፈራ ይመሰክራሉ፡፡ “እኔም ልጅ አለኝ፡፡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ የትራፊክ አደጋ እንዳይደርስባቸው ተጠብቀው በጥንቃቄ እንዲሻገሩ ከሚያደርጉት መልካምነት ሁሉም ሊማር ይገባል፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጎ ፈቃድ ባህል እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ቢኒያም ጊቻ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ ግንዛቤ ማስረፅ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ባለፉት አስር ወራት በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃድ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ፣ ልበ ቀና ባለሀብቶች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የግልና የመንግስት ተቋማት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የስራቸው አካል አድርገው በሰሩት ስራ ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ያስረዳሉ፡፡

አዲስ አበባ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተሻለ የበጎ ፈቃድ ስራ እየተከናወነባት ያለች ከተማ ናት የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ በጎ ፈቃድ ባህል እንዲሆን የሚሰራው ስራ ግንዛቤ ከማስረፅ ይጀምራል፡፡ ከዚህ አንፃር መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም፣ መድረኮችን፣ የፓናል ውይይቶችን በማዘጋጀት፣ የተሰሩ ስራዎችን በማስተዋወቅ፣ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ቀንን በማክበርና የተለያዩ ኹነቶችን በመጠቀም ከ285 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ ተችሏል፡፡ በከተማዋ በሚገኙ ከ402 በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ የበጎ ፈቃድ ክበባት ተቋቁመው ተማሪዎች በጎ ፈቃድን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲማሩ፣ እርስ በርስ መረዳዳትና መደጋጋፍን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ስራ ከስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲሰራበት የቆየ ሲሆን፤ በዘንድሮው  ዓመት  በተለየ  ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ አቶ ቢኒያም ይናገራሉ፡፡

የከተማዋን ነዋሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በበጎ ፈቃደኝነት በማሳተፍ ረገድ ውጤታማ ስራ መከናወኑን አቶ ቢኒያም ያነሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ክረምት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት ሲሆን፤ በድግግሞሽ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ከ62 ሺህ በላይ፣ በከተማዋ በሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለተገልጋዮች አቅጣጫን በማመላከት፣ አስታማሚ የሌላቸውን ታካሚዎች በማስታመምና መሰል “በጎነት በሆስፒታል” አገልግሎት ከ3 ሺህ 500 በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል፡፡

የጎርፍ ስጋትና ለመከላከል የመፋሰሻ ቱቦዎችን በማፅዳት ከ541 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በየአካባቢያቸው በድግግሞሽ ተሳትፈዋል፡፡ ሌላው በርካታ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ እያደረጉበት ያለው የማዕድ ማጋራት ሲሆን፤ ከባለሀብቱ ድጋፍ በማሰባሰብና ለተጠቃሚዎች በማድረስ በጉልበት አስተዋጽኦ በማድረግ ከ73 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

የቤት እድሳት ላይ በዋናነት የሚታደሰውን ቤት በማፍረስ፣ እቃዎችን በአግባቡ በማውጣትና የሚፈለገው ቦታ በማድረስ የጉልበት አስተዋፅኦ በማድረግ ረገድ ከ63 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ 

የመንገድ ትራፊክ ማስተናበር ሌላኛው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሆን፤ በዚህ ዘርፍ የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች በተለይ ክረምት ላይ ቁጥራቸው ከፍ ይላል፡፡ በበጋ ወቅት ይህንን ስራ የሚያከናውኑ በመደበኛነት የመንገድ ትራፊክ ማስተናበር ላይ የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች 800 ናቸው፡፡ ክረምት ላይ ተማሪዎችም ስለሚሳተፉ በጥቅሉ 8 ሺህ አካባቢ በጎ ፈቃደኞች ይደርሳሉ።

በ“ሙያዬን ለሀገሬ” መርሃ ግብር መምህራንን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ11 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በሰላም እሴት ግንባታ፣ በኪነ ጥበብና መዝናኛ ፕሮግራም፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በወሰን የለሽ በጎ ፈቃድና በሌሎች ፕሮግራሞች በርካታ በጎ ፈቃደኞች እየተሳተፉ እንደሚገኙም አቶ ቢኒያም አብራርተዋል፡፡

በጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲሆን ለበጎ ፈቃደኞች እውቅናና ሽልማት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ባለፉት አስር ወራት ከ6 ሺህ 900 በላይ ለሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ከምስክር ወረቀት ጀምሮ እስከ ዋንጫ የሚደርስ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡

አቶ ቢኒያም እንደገለፁት፣ ባለፉት አስር ወራት ውስጥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ 7 ሺህ 566 የሚሆኑ ቤቶች ታድሰውና ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡ በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ የበጎነት መንደሮች በየቦታው ተገንብተዋል፡፡ በእነዚህ በታደሱ ቤቶችም ከ29 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ሌላው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰፊ የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሆነበት የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ሲሆን፤ ባለፉት አስር ወራት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም በተለያዩ በዓላት በድግግሞሽ ድጋፍ የተደረገላቸውን በማካተት ጭምር እንደሆነ አቶ ቢኒያም አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እየተጠናከረ የመጣው በጤናው ዘርፍ የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሌላኛው ሲሆን፤ በዚህም ከ123 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የነፃ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ትላልቅ የህክምና ካምፖችን አደባባዮች አካባቢ በመገንባት ከምርመራ እስከ ህክምና የሚደርስ አገልግሎት ነዋሪዎች የሚያገኙበት፣ ትላልቅ የመንግስት፣ የግልና ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት የሚሳተፉበትና ውጤትም የተገኘበት መርሃ ግብር እንደሆነ አቶ ቢኒያም አንስተዋል፡፡

ሌሎች በዚህ ዘርፍ ያላካተትናቸው የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብርም በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አቶ ቢኒያም አብራርተዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ በተሰጡ አገልግሎቶች ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግስት ይሸፈን የነበረን ወጪን ማዳን አስችሏል። አቶ ቢኒያም እንደገለፁት፣ በበጎ ፈቃድ በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ሁሉም ስራዎች ተለቅመው ቢያዙ ከዚህም በላይ ይሆናሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በበጎ ፈቃድ የሚሰጡ አገልግሎቶች በይዘትም ሆነ ብዛት እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰኔ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ ከከተማዋ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞች በድግግሞሽ በ15 ፕሮግራሞች እና በ19 መርሃ ግብሮች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ 800 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከሰኔ 5 ቀን እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉ 90 ቀናት በልዩ ተልዕኮ ከሚያከናውናቸው 18 ዋና ዋና ተግባራት መካከል የክረምት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review