AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም
የውጭ ባንኮች እንዲሳተፉ የሚፈቅደው የባንክ ስራ አዋጅ ኢትዮጵያ የፈረመችውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማሳለጥና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ አቡሌ መሀሪ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፋይናንስ ዘርፉን በእውቀትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ኢኮኖሚው ከዓለም ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ለማሳደግ መንግስት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ የዘርፉን ተወዳዳሪነት በማሳደግ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ያለመ የባንክ ስራ አዋጅ ጸድቆ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 አጽድቋል፡፡
አዋጁ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚሆንበትን ስርዓት የዘረጋ ነው።
የውጭ ባንኮች እና አልሚዎች በፋይናንስ ዘርፉ ሲሰማሩ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ያለው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ያስችላቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ከፍተኛ ተመራማሪ አቡሌ መሀሪ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት የሚያቀላጥፍ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች እንዲሳተፉ ፈቃድ ሲያገኙ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ካፒታል ይዘው እንደሚመጡ የገለጹት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው፤ የባንክ አገልግሎት የማያገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለሥራ እድል ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የፈረመችውን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በማሳለጥ፣ ባንኮች ከመጡባቸው ሀገራት ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በማጠናከር ጠንካራ ኢኮኖሚ መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለሀገር ውስጥ ባንኮች ተስፋም ስጋትም መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው፤ የበለጠ ትርፋማ ለመሆን የገጠሩን ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ ተደራሽ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባንኮች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የካፒታል ገበያ የፈጠረላቸውን እድል በመጠቀም አቅማቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡