የባዛር ግብይት በሕጋዊ የንግድ ስርዓት

You are currently viewing የባዛር ግብይት በሕጋዊ የንግድ ስርዓት

በዓላት ተናፋቂዎች ናቸው። ለመናፈቃቸው ብዙ ምክንያቶች አሏቸው። በዓላት፤ ግርማና ሞገስ መላበሳቸው፣ ከዋዜማቸው ጀምሮ መዳረሻቸውን የሚያሳውቅላቸውን አጃቢ መታደላቸው፣ ድምቀት እና ውበት መጎናፀፋቸው፣ በማዕድ የተትረፈረፈ ገበታ እና በመጠጥ የተሞላ ዋንጫ በየቤቱ የሚጠብቃቸው፣ የክት ወይም አዲስ አልባሳት የሚሰናዳላቸው  መሆናቸው ከዘወትር ቀናት ይለያቸዋል። የበዓላት እንኳን ዕለታቸው ዋዜማቸው ይናፈቃል። የበዓላት ምሉዕነት በዋዜማቸው በሚደረግ መሰናዶ ይወሰናል። የዋዜማው እና ከዋዜማው አስቀድሞ ባሉት ቀናት የሚደረገው መሰናዶ የሚወሰነው በአብዛኛው በገበያ ሥፍራዎች በሚስተዋል ሁለንተናዊ (የምርት ዓይነት፣ አቅርቦት፣ ዋጋ፣ ጥራት…) ነው፡፡

የግብይት ሥፍራዎች የበዓላት ዋዜማዎች ጌጦች ናቸው ማለት ይቻላል። የግብይት ሥፍራዎች የበዓላት ዋዜማ ድባብ፤ የበዓላትን መዳረስ እንደሚጠቁሙ ከዋክብት ይቆጠራሉ። ሌላውን ትተን የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊያን መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ በበዓላት ዋዜማ የሚታየውን የግብይት ሥፍራዎች ድባብ ካስተዋልን፤ የደማቆቹ በዓላት ፈርጦች መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ከሰሞኑ እንኳን፤ ከትናንሽ የችርቻሮ ሱቆች እስከ ትላልቅ የግብይት ማዕከላት፣ ከጉሊት እስከ ሰፋፊ የአደባባይ መገበያያዎች(ባዛሮች) ዓይነቱ በበዛ ምርት ተጨናንቀው የግብይት ተዋናዮችን በማስተናገድ ሁነት ላይ እንደሚገኙ እየተመለከትን እንገኛለን። እርጥብ ሳሩ፣ ቅቤ ማሩ፣ እንቁላል ዶሮው፣ ሙክት ሰንጋው፣ ስንዴ ጤፉ፣ ጫማ ልብሱ፣ ጌጣጌጡ … በግብይት ሥፍራዎች ወጥተው ሸማቹን ወደ ነጋዴው በመግነጢሳዊ ኃይላቸው እየሳቡ፣ እያነጋገሩ፣ እያከራከሩ፣ እያስወሰኑ በሁሉም አካባቢዎች ያሉት የግብይት ሥፍራዎች እንዲደምቁ (እንዲደሩ) አስችሏቸዋል፡፡

የባዛር ግብይቶች ገበያን ከማረጋጋት ባሻገር ፋይዳቸው የጎላ ነው

የበዓላት ወቅት ሲመጡ አስፈላጊ ምርቶችን ለመግዛት ወደ ባዛሮች ጎራ ማለትን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ የገለፁልን የአዲስ አበባ ከተማ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ነዋሪዋ ወይዘሮ ትዕግስት አሰፋ ሲሆኑ፤ የሚፈልጓቸውን ምርቶች በአንድ ሥፍራ በብዛት እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙባቸውን ዕድል መፍጠራቸው ባዛሮችን ለመምረጣቸው በምክንያትነት አንስተዋል፡፡ ከባዛሮች በሚፈፅሟቸው ግብይቶች የሚፈልጓቸውን ምርቶች ማግኘት ቢችሉም በእነዚህ የግብይት ሥፍራዎች በሚፈፅሟቸው ግብይቶች ለከፈሉበት ደረሰኝ የመቀበል ልምድ እንደሌላቸው አልሸሸጉም፡፡ በባዛሮች ላይ የሚታየው የሰው መብዛት፣ የተጨናነቀ ሁኔታ መፈጠር፣ ስለምርቱ ግዢ እንጂ ስለደረሰኝ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን በግዢያቸው ላይ ደረሰኝ ላለመቀበል ያስቻላቸውን ሁኔታ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ የገና በዓል ለግብይት ጎራ በሚሉባቸው ባዛሮች ግን ግዢ ለሚፈፅሙባቸው ምርቶች ደረሰኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡

በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) በዓልን የአዲስ አበባ ነዋሪ ህብረተሰብ በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፍ ከመደበኛ የግብይት ሥፍራዎች በተጨማሪ፤ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ባዛሮች ተሰናድተዋል፤ በመሰናዳትም ላይ ናቸው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጁትን እና በመዘጋጀት ላይ ያሉ ባዛሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በማስተባበር እና በመምራት ተግባር ላይ የተለያዩ ተቋማት ማለትም፡- ገቢዎች ቢሮ፣ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን፣ ንግድ ቢሮ፣ የአርሶ አደር መልሶ ማቋቋምና ከተማ ግብርና ኮሚሽን፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በዋናነት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ 

የእነዚህ ተቋማት የመቀናጀት ዋና ዓላማ፡- በተትረፈረፈ ምርት የተሞሉ የባዛር ገበያዎች ለበዓሉ አስፈላጊ በሆኑ ምርቶች እንዲሞሉ እና ግብይታቸው የሰመረ፣ በሕግና ሥርዓት የተመራ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ በየአካባቢው እና በትላልቅ የገበያ ማዕከላት የተሰናዱ ባዛሮች ዓላማቸውን እንዲያሳኩ እና የመዲናዋ ነዋሪ በአቅሙ አስፈላጊውን ነገር ገዝቶ በዓሉን በቤቱ ማክበር እንዲችል በንቃት ከሚሳተፉት መካከል በከተማዋ የሚገኙ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት ለበዓላት ብቻ ሳይሆን፤ በሌላውም ጊዜ ለሸማቹ ማህበረሰብ መሰረታዊ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በማቅረብ በገበያው ላይ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የገናን በዓልም ምክንያት በማድረግ ከመደበኛው ተግባር በተጓዳኝ ለበዓል የሚያስፈልጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በባዛሮች ላይ ይዘው ለመቅረብ መሰናዷቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ሃብተየስ ዲሮ፤ በመዲናዋ ያሉ 11 የሸማች የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና በሥራቸው ያሉ 150 መሰረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት በዓሉን አስመልክቶ በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ እና ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም እንሰሳት እና የእንሰሳት ተዋፅዕዎች በብዛት ተገዝተው ለሸማቾች ለማሰራጨት ተዘጋጅተዋል። ከምርቶቹ መካከል ጤፍ(18 ሺህ 931 ኩንታል)፣ የስንዴ ዱቄት(16 ሺህ 370 ኩንታል)፣ ቀይ ሽንኩርት(15 ሺህ ኩንታል)፣ ዶሮ(7 ሺህ 933)፣ እንቁላል(2 ሚሊዮን 58 ሺህ)፣ ቅቤ(17 ሺህ 800 ኪሎ ግራም)፣ አይብ(10 ሺህ 150 ኪሎ ግራም)፣ ለቅርጫ የሚሆን እና በልኳንዳ ቤት የሚቀርብ በሬ(2 ሺህ 16)፣ ፈሳሽ ዘይት(1 ሚሊዮን 964 ሺህ 500 ሊትር) ተገዝቷል፡፡ በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለሸማቹ ማህበረሰብ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡

“የሸማች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ለበዓሉ የሚሆኑ ምርቶችን ከአምራች አርሶ አደር ዩኒየኖች፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ከግል ድርጅቶች፣ ከአስመጪዎች ግዢ ተፈፅሟል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ሃብተየስ፤ ይህ ሥራ ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ በዕቅድ መከናወኑን አስታውሰዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው የምርት ግዢ የተፈፀመው በሕጋዊ የደረሰኝ ግብይት መሆኑን ጠቁመዋል። ምርቶቹን ከታህሳስ 21 እስከ 28 ድረስ በክፍለ ከተሞች በሚዘጋጁ ባዛሮች፣1 መቶ 32 በሚሆኑ የእሁድ ገበያዎች፣ በሸማች ህብረት ሥራ ሱቆች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባሉም ብለዋል። በበዓሉ ዕለትም በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ስር በሚተዳደሩ 239 ሥጋ ቤቶች አንድ ኪሎ ስጋ ከ 400 እስከ 520 ብር ድረስ የሚሸጥ ይሆናል። በአጠቃላይ በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት የሚቀርቡ መሰረታዊ ምርቶች በነጋዴው ከሚቀርቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጥራታቸው ሳይጓደል፤ በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው በማወቅ ሸማቹ ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባው አሳውቀዋል፡፡

በዓላትን ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ የግብይት እንቅስቃሴዎች ከሚደረግባቸው ሥፍራዎች መካከል ባዛሮች ይጠቀሳሉ፡፡ የባዛር ግብይቶች በከተማ ደረጃ እንደ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ በመርካቶ እና ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ትላልቅ የንግድ ማዕከላት፣ አደባባዮች እና ለግብይቱ ምቹ በሆኑ ሥፍራዎች እንደሚከናወኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች ያሳያሉ፡፡ በባዛሮች ላይ ምርታቸውን ለሸማች ይዘው በመውጣት የሚያስተዋውቁ እና ሽያጭ የሚፈፅሙ በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ግብይቶች ሕጋዊ አግባብን በተከተለ መልኩ፣ ደረሰኝ እየተቆረጠላቸው እንዲከናወኑ እንደከተማ አስተዳደር እየተደረገ ያለው የክትትል እና ቁጥጥር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ሃሳብ እንዳብራሩት፤ በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ የንግድ እና ግብይት ሂደቶች በስርዓት እና በሕግ አግባብ  እንዲከናወኑ የገቢዎች ቢሮ በትኩረት ይሠራል፤ እየሠራም ይገኛል። በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ የሕግ ተገዢ ሆኖ ግብይቶችን እንዲፈፅም ተቋማዊ ኃላፊነቱን ይወጣል።

ግብይት በደረሰኝ እንዲከናወን ከዚህ ቀድም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ተፈፃሚ እንዲሆን ከመስከረም ወር 2017 ጀምሮ እየተሄደበት ያለው የአሠራር ስርዓት ውጤት በማምጣት ላይ ነው፡፡ የደረሰኝ ግብይት እንዲፈፅሙ ሕጋዊ ግዴታ ያለባቸው በደረጃ “ሀ” እና በደረጃ “ለ” ግብር ከፋይነት ደረጃ ላይ የተመዘገቡ ሲሆን፤ አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች እና አምራቾች ላይ በዋናነት ያተኮረ ይሆናል፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ያለው ግብይት ሕጋዊነትን ከሚያረጋግጡ ተግባራት አንዱ የሆነው የደረሰኝ ግብይት በአግባቡ ተፈፃሚ ማድረግ ወሳኝነት አለው፡፡ ቢሮውም በዋናነት በአምራች፣ በአስመጪ እና በአካፋፋዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ ወደ ባዛር የሚወጡ ምርቶች መነሻቸው ከአምራቾች፣ ከአስመጪዎች ወይም ከአከፋፋዮች ነው። እነዚህ ደግሞ ግብይታቸውን በደረሰኝ ብቻ እንዲያከናውኑ ሕጋዊ ግዴታ የተጣለባቸው ናቸው። ስለሆነም ግብይታቸውን በሱቅ በሚፈፅሙ ወቅት የሚከተሉትን   በደረሰኝ   የመገበያየት    አሠራር በባዛሮች ላይ መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ የግብይቱን ሁኔታ የሚለየው የቦታ እንጂ የሕጋዊ አሠራር ለውጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ በባዛሮች ላይ የሚፈፀሙ ግብይቶች በደረሰኝ እንዲሆኑ የንግድ ቢሮ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በዓላትን መሰረት በማድረግ ለሸማች ምርቶቻቸውን ይዘው በመውጣት ለሸማቾች የሚያቀርቡ በግል ወይም በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር በመደራጀት የሚንቀሳቀሱ አምራቾች ሆነው ግብይት መፈፀም ያለባቸው በደረሰኝ እንደሆነ ሕጉ ያስቀመጠውን አሠራር ተፈፃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ማብራሪያ መሰረት፤ በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚከናወነው በዓላትን መሰረት ያደረገ ግብይት በደረሰኝ  እንዲከናወን  እንደማዕከል  የአዲስ  አበባከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮን ጨምሮ፤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና የቦሌ ክፍለ ከተማ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከሚመለከተው የፌደራል ተቋም ጋር በመተባበር የክትትል እና ቁጥጥር ተግባሩን ያከናውናል፡፡ በተመሳሳይ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች በኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ የሚከናወኑ ግብይቶች በደረሰኝ እንዲፈፀሙ በአቅራቢያቸው ያሉ የክፍለ ከተማ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች፣ የማዕከል እና የፌደራል አካላት በመቀናጀት ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በግብይት ላይ የሚሳተፉ አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ግብይታቸውን በደረሰኝ መፈፀም እንዳለባቸው በማወቅ ተግባራዊ ማድረግ እና የሕግ ተገዢነትን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሸማቾቹም ግዢ ለፈፀሙት ምርት ወይም አገልግሎት ደረሰኝ መጠየቅና መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ የደረሰኝ ግብይት በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በመንግስት በከፍተኛ ትኩረት የመፈፀሙን ፋይዳ ነጋዴውም ሆነ ሸማቹ ማህበረሰብ በአግባቡ መገንዘብ አለባቸው፡፡

“በከተማዋ የተረጋጋ የግብይት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የዋጋ ንረት እና የምርት አቅርቦት እንዲቀንስ በማሰብ የእሁድ ገበያዎችን ጨምሮ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት፣ ድጋፎችን በማድረግ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት በመደጎም ምርቶች ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሱ የከተማ አስተዳደሩ በስፋት እየሠራ ይገኛል” ያሉት የገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር፤ በዓላትን መሰረት በማድረግ በየአካባቢው በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ የሚያቀርቧቸው ምርቶች ላይ በሚፈፅሙት ግብይት ደረሰኝ መቁረጥ ላይጠበቅባቸው እንደሚችል በማስታወስ፤ የደረሰኝ ግብይት ሥርዓቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በዋናነት  በደረጃ “ሀ” እና በደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ላይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡

በንግድ ባዛሮች ላይ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ዕቃዎች ለሸማቾች ይቀርባሉ፡፡ ትላልቅ አስመጪዎች፣ አምራቾች፣ አከፋፋዮች እና ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ይሳተፋሉ ያሉት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣዕ ሀብት ምሁር ዘካሪያስ ሚኖታ(ዶ/ር) ሲሆኑ፤ በእነዚህ ባዛሮች ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች(አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች) አቅርቦቶቻቸውን የሚያሳዩበት መድረክ በመፍጠር በከተማዋ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ  በማበረታታት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት ከመቅረባቸውም ባሻገር ማህበረሰቡ ለሀገር ውስጥ ምርት ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችም እንዲበረታቱና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫም ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የባዛሮቹን ፋይዳ ከኢኮኖሚ አንፃር ስንመዝነው ጥቅሙ ትልቅ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፤ ለአብነትም በባዛሮች አምራቾች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ከሸማቹ ጋር የሚገናኙባቸው መድረኮች በመሆናቸው  የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማሳጠር የተረጋጋ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡ ይህም የኑሮ ውድነቱ ረገብ እንዲል ማድረጊያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ባዛሮቹ  ከትላልቅ ኩባንያዎች እስከ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የተለያዩ የገበያ ተሳታፊዎችን በማቀናጀት ጤናማ ውድድርን ለመጨመር ይረዳል፡፡ እርስ በእርስም የልምድ ልውውጥና ትብብርን ለመፍጠር ማስቻሉንም ገልፀዋል፡፡

እነዚህ በባዛር የሚከናወኑ ግብይቶች ህጋዊ መሆናቸውን፣ በትክክልም የታለመላቸውን አላማ እያሳኩ መሆናቸውን እና ይበልጥም ሸማች ማህበረሰብ ተጠቃሚ ስለመሆኑ መፈተሽ እንደሚገባ የጠቆሙት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፤ ይህንን መስመር ለማስያዝ የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል ባሻገር ሸማቹ ማህበረሰብም ችግሮቹን በመጠቆምና ሕጋዊ ግብይትን ምርጫው በማድረግ ተባባሪ መሆን እንደሚገባውም ጠቅሰዋል። የከተማ አስተዳደሩ ተሳታፊ የሆኑ ነጋዴዎችን መመዝገብ እና የታክስ ህጎችን እንዲከተሉ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን በበዓል ሰሞን ሰፊ የሆነ የንግድ ልውውጥ ስለሚኖር ባዛሮቹ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እምርታ ያላቸው አበርክቶ ከፍ እንዲል በር ይከፍታል፡፡

በተለይም ይላሉ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ በንግዱ ዘርፍ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን  በባዛሮች ላይ የበለጠ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡ ይኸውም በርካታ ህዝብ ስለሚያስተናግዱ ሁሉም ስለሕጎቹ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን በአዘቦት ቀናትም ሁሉም ሕግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ግንዛቤ ስለሚፈጠር እንደ ከተማ ያለውን ንግድ ስርዓት የበለጠ ጤናማ ለማድረግ ያግዛልም ብለዋል የምጣኔ ሀብት ምሁሩ።ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በደረሰኝ ግብይት ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት ወደ ሥርዓት ለማስገባት ከወርሃ መስከረም 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በስፋት እና በትኩረት እየሠራበት ይገኛል፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ በነበሩት ጊዜያት ከማዕከል እስከ ታች ድረስ ባሉት የገቢ ሰብሳቢ ተቋም መዋቅር እና አደረጃጀት እንዲሁም በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከተዋቀረ ግብረ ሃይል ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በደረጃ “ሀ” እና በደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ የተመዘገቡ አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ላይ በዋናነት በማተኮር እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ ሥራ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን ያለፉትን የግብይት እንቅስቃሴዎች ሁሉ የተመለከተ ነው፡፡ መረጃዎችንም ከሦስተኛ ወገን በመውሰድ እስከመጠቀም የደረሰ ነው፡፡ የከተማዋ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ ሰፊ እና ግዙፍ የግብይት ማዕከል እንደሆነ በሚነገርለት መርካቶ ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራውን ወደ ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች እንዲሰፋ ተደርጓል። በዚህም አበረታች ውጤት መጥቷል፡፡ ለማሳያነት በወርሃ ሕዳር ብቻ 1 ሺህ 145 የሚደርሱ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈፅሙ እና በመሰል ሕገ ወጥ የግብይት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው ተገቢ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

“ከሕጋዊ የግብይት ሥርዓት በመውጣት በሚፈፀም ግብይት ተጠቃሚዎች የሚሆኑት ሕገወጥ ግለሰቦች ሲሆኑ፤ በአንፃሩ መንግስት እና ሕዝብ ተጎጂዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያለደረሰኝ በሚፈፀም ሕገወጥ የግብይት ሂደት ውስጥ መንግስት ማግኘት ያለበትን ገቢ ያጣል። ከተማዋን ብሎም አገርን ለማልማት እና ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በዕቅዱ መሰረት ለመፈፀም ኢኮኖሚያዊ አቅም ይቀንሳል። ሕዝብም ከመንግስት ማግኘት የሚገባውን ልማት እና አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኝ ያደርጋል። ጥቂት ሕገወጦች ተጠቃሚዎች፤ ብዙዎች ደግሞ ተጎጂዎች የሚሆኑበትን ኢፍትሃዊነት ይፈጥራል” ያሉት በገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሠውነት አየለ፤ የደረሰኝ ግብይቱ እየተሻሻለ እንደሚገኝ በመጠቆም በሕገወጦች ጫና ምክንያት ከገበያ ሥርዓቱ ወጥተው የነበሩ ነጋዴዎች ወደ ንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review