የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ህዝባዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግ ጋር ተወያዩ

You are currently viewing የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ህዝባዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግ ጋር ተወያዩ

AMN- ጥቅምት 20/2017 ዓ.ም

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ህዝባዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግ ጋር ተወያይተዋል።

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን እየመሩ በቻይና የሚገኙት አቶ አደም ፋራህ ኢትዮጵያና ቻይና በመተማመን እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ግንኙነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅት ቻይና የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ የሰው ኃይል እና ኮንትራቶች ምንጭ መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ አነስተኛ ወለድ ብድር እንዲሁም ኢምፖርትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ መሆኗን ያነሱ ሲሆን በርካታ የኢትዮጵያ ምርቶችም በቻይና ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን በመልካምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በበርካታ ጉዳዮች አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደሆነ የገለጹት አቶ አደም፣ በተለይም የህዳሴ ግድብ ግንባታን 97 ከመቶ ማድረስ፣ ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ፣ በአረንጓዴ አሻራ በስድስት አመታት በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን መትከልና ሌሎችም ዋና ዋና ስኬቶችን አንስተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የቻይና ህዝባዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግ በበኩላቸው ቻይና እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ከመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ ትብብራቸውን በየጊዜው እያሳደጉ መምጣታቸውን በማውሳት በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ ደረጃ መድረሱን አስታውሰዋል።

በተለይም ወሳኝ በሆኑ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የጋራ መርህና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርገው እየሰሩ እንደሆነ መግለጻቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በቀጣይም ከሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በተጨማሪ በቻይና አፍሪካ ፎረም፣ በሮድ ኤንድ ቤልት፣ በብሪክስ እና ሌሎች ባለብዙ ወገን መድረኮችም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበወዋል።

አቶ አደም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ላደረጉት አስተዋጽኦ የቻይና መንግሥትን አመስግነው፣ የሁለቱን ሀገራት የመንግስት ለመንግስትና የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችሉ ሀሳቦችን አንስተዋል።

በዚህም መሠረት በንግድና በኢንቨስትመንት ማስፋፋት አብረው እንዲሰሩ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ሎሎች የመፃዒ ቴክኖሎጂ መስኮች የእውቀት ሽግግርን ማዕከል ያደረገ ትብብር እንዲመሰረት እና በተለይም በቡና የተጀመረውን ኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ቻይና ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት በአይነትም ሆነ በመጠን ለማሳደግ የቻይና መንግስት አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር እና ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

እንዲሁም በቀጠናዊ ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴዎችና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ለመተባበር ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ሀሳብ ማቅረባቸውም ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ የብልጽግና ፓርቲ ከወራት በኋላ በሚያደርገው ሁለተኛ ጉባዔ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።

የቻይና ህዝባዊ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ሊ ሆንግዦንግም የተነሱትን የትብብር መስኮች መቀበላቸውን በመግለጽ በጋራ ለመስራትና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመጨረሻም የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛው ጉባዔ ግብዣውን መቀበላቸውን እና ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸው መሆኑን መግለጻቸውን በመረጃው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review