የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኢንስፔክሽና ሥነ ምግባር ኮሚሽን አመራሮች ጋር ውይይት አደረገ

You are currently viewing የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኢንስፔክሽና ሥነ ምግባር ኮሚሽን አመራሮች ጋር ውይይት አደረገ

AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የኢንስፔክሽና ሥነ ምግባር ኮሚሽን አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በቤጂንግ የሚገኘውን የልዑካን ቡድን የሚመሩት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ጠንካራ ፓርቲ ለመመስረት ጠንካራ የሥነ ምግባር እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ብልጽግና ፓርቲ የውስጥ ቁጥጥሩን ለማጠናከር በርካታ ስራዎችን መጀመሩንና ከዚህ አንጻር የረጅም ጊዜ ልምድ ካለው ሲፒሲ ተጨማሪ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የሲፒሲ የሥነ ምግባር ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አመራር የሆኑት ዋንግ ሺንቺ በሲፒሲ የውስጥ ኢንስፔክሽን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት፣ የኮሚሽኑን ተግባራትና ኃላፊነቶች፣ ያከናወናቸውን ሥራዎች እና የአሰራር ሥርዓቱን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አንድ ፓርቲ ለሕዝብ ለገባው ቃል ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል እና በተለይም የአባላቱ ብዛትም ሆነ የፓርቲው መዋቅር እየሰፋ ሲሄድ ውጤታማነትን ከግልጽነትና ተጠያቂነት ጋር አስጠብቆ ለመቀጠል የውስጥ ሥነ ምግባር እና ቁጥጥር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ አባላትን በማፍራት መዋቅሩን እያስፋፋ መሆኑን በማንሳት አባላቱ በሥነ ምግባር ታንፀው ሕዝብን እንዲያገለግሉ ሰፊ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም በጉባዔ የተመረጠና ከላይ እስከ ታች የተዋቀረ ጠንካራ የሥነ ምግባር እና የኢንስፔክሽን ኮሚሽን እየተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

በልዑካን ቡድኑ አባላት በርካታ ሃሳቦች እና የማብራሪያ ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት መደረጉን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review