ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላ ሀገሪቱ ከተውጣጡ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ የምንፈልገው አካታች የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ 273 ሰዎች በተለያዩ የአመራርነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከነዚህም መካካል 4 ሚኒስትሮች፣ 4ቱ ደግሞ ሚኒስትር ዴኤታዎች ሲሆኑ የተቀሩት በቢሮ ኃላፊ እና በተለያዩ የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ውስጥ ተካተው እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ደረጃ መንግስት ተፎካካሪዎችን አሳታፊ ያደረገ አካሄድ መከተሉ የፖለቲካ ምህዳሩን በተግባር ማስፋቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
የብልፅግና ዕሳቤ በፉክክርና ትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፉክክር ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርግም ነው የገለፁት፡፡
አሁን ባለው መንግስት ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካተት መቻላቸውም በእኛ በኩል ለትብብር በቂ ቦታ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመንግስትም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲ በኩል ኢትዮጵያ አንድ ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትወጣ ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ጤናማ ፉክክርና ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን አብራተዋል፡፡
መንግስት የትብብርን አስፈላጊነት ከጅምሩ በፅሁፍ ያሰፈረዉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፅሁፍ ያስቀመጠውን ደግሞ መተግበር መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም በመንግስት በኩል ለትብብርና ፉክክር ዝግጁነት እንዳለ አስታውቀዋል፡፡