AMN -ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም
የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ሰኞ ለ17ኛ ጊዜ በመላው ሀገሪቱ ይከበራል፡፡
በዓሉ በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦ በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ ቀጣይነት ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያሳያል፡፡
ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ያለንን እውነተኛ ክብርና ፍቅር ሁላችንም እንደዜጋ የምንገልፅበትና ለዚህም በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በየኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓለማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ-ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡