AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ማጎልበት ማስቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት 19ኛውን የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “አገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ አክብረዋል፡፡
በዓሉ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ በሚገነባ መልኩ መከበሩም ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን አብሮነትና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያን ብዝሃ ማንነት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዓለም የሚያስተዋውቅ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም የእርስ በርስ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ኢትዮጵያ በብዝሀ ማንነቷ የደመቀች ሆና እንድትቀጥል ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበረው ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ባስመዘገበችበት ወቅት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የለውጡ መንግስት አሳታፊና አካታች ሥርዓት በመዘርጋት የዜጎችን የመልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ችግሮችን በመደመር እሳቤ በመፍታት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነትን በማረጋገጥ የበለጸገች ሀገር እውን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የላቀ ትብብር ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡