የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ለሀገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው- አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

AMN – ህዳር 22/2017 ዓ.ም

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ለሀገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል፡፡

አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር ለሀገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው ብለዋል።

በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእርስ በርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ መሆን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የክልሎች መሠረተ-ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ብሎም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

ሰላሟ የፀናና የበለፀገች ሀገርን ለመፍጠር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲጠብቁም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review