የብዙዎች ተስፋ፡- ኮዲንግ

እንደ መግቢያ

አንደርስ ሄይልስበርግ ከኮዲንግ (Coding) ጋር በተያያዘ ሥሙ ይታወቃል፡፡ በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር በወርሃ ታኅሣሥ 1960 የተወለደው ዴንማርካዊው ሊቅ ለሂሳብ እና ፊዚክስ ትምህርቶች የተለየ ተሰጥዖ እና ፍቅር እንደነበረው ግለ ሕይወቱን የሚያስረዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርቱን በዴንማርክ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ተከታትሏል። ከኮምፒዩተር ቀመር (ኮዲንግ) ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ማሰላሰልና መመርመር የጀመረው ገና በማለዳው ነበር፡፡ በዚህም Turbo Pascal (ቱርቦ ፓስካል) የተሰኘ ለሶፍትዌር ልማት ስርዓት እና ማጠናቀር አጋዥ የሆነ የፓስካል ፕሮግራሚንግ ቋንቋ ፈጠረ። ሌሎችንም መሰል ሥራዎች አከታትሎ ከወነ፡፡

የወጣቱን አቅም የተረዳው የማይክሮሶፍት ኩባንያ በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር በ1996 ኩባንያውን እንዲቀላቀል አደረገው፡፡ ዕምቅ አቅሙን አሟጥጦ እንዲያወጣ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረለት፡፡ ኩባንያውን ብቻ ሳይሆን ለዲጂታሉ ዓለም እጅግ ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ የኮምፒዩተር ቀመሮችን (ኮዲንግ) ማበርከቱን ቀጠለ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በማይክሮሶፍት የበይነ መረብ ስነ ምህዳር ውስጥ (Microsoft .NET ecosystem) ወሳኝ ሚና ያለው የC# ፕሮግራሚንግ ቋንቋ፣ ለኮምፒዩተር ፅህፈት አገልግሎት ቁልፍ አስተዋፅኦ ያበረከተውን የጃቫ ስክሪፕት (Java Script) መተግበሪያን፣ ለትልልቅ ተቋማት የሚያገለግሉ፣ የድረ- ገፅ አገልግሎት የሚሰጡ (web services) እና የኮምፒዩተር ጨዋታዎችን ማልማት (game development) የሚያስችሉ ወሳኝ ቀመሮችን (ኮዲንግ) ፈልስፎ ለዘርፉ ዕድገት አበርክቷል። እነዚህና መሰል ሥራዎቹ በፕሮግራሚንግ ቋንቋዎች እና በሶፍትዌር ማበልጸጊያ መሳሪያዎች ፈጠራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ሥማቸው ከሚጠራ ሊቆች አንዱ አድርገውታል፡፡

በተመሳሳይ የሊኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም (Linux operating system) በመፍጠር የሚታወቀው ፊንላንድ- አሜሪካዊ የሶፍትዌር መሐንዲስ ሊኑስ ቶርቫልድስ ነው። በፊንላንዷ ከተማ ሄልሲንኪ በጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር ታኅሣሥ 28 ቀን 1969 የተወለደው ሳይንስ ሊቁ፤ የኮምፒውተር ሶፍትዌር ማበልፀጊያ ቀመሮችን መሥራትና ጥቅም ላይ ማዋል የጀመረው ገና የከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ ነበር፡፡ በወቅቱም ወሳኝ የሆነውን የሊኑክስ ከርነል ፕሮጀክት ቀርጿል። ፕሮጀክቱን በሂደት በማሻሻልና በማሳደግ አንድሮይድን ጨምሮ፤ የበርካታ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች የሚንቀሳቀሱበትን  የሊኑክስ ከርነል (Linux kernel) ዕውን በማድረግ ለአብዛኛው የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ሰፊውን እና ውስብስቡን አገልግሎት ለማስተዳደር እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ላሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች በአስተማማኝ ሁኔታ አገልግሎቱን ለማድረስ ካለሊኑክስ የሚታሰብ አይደለም፡፡

  ኮድ የማድረግ ተግባር (Coding)

ኮድ የማድረግ ተግባር (Coding) ኮምፒዩተሮች የተወሰኑ እና የተለዩ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ መመሪያዎችንና አሠራሮችን የሚሰጡ የፕሮግራሚንግ ቋንቋዎችን (programming language) የመፍጠር ብቃትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህንን መሰል ተግባር በብቃት የሚፈፅሙ ሠዎች ኮደርስ (Coders) ይባላሉ፡፡ ሙያተኞቹ፤ ፕሮግራመሮች (programmers) ወይም አልሚዎች (developers) በመባል እንደሚጠሩ በተለያዩ ገፀ- ድሮች ላይ የሰፈሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በወርሃ ሐምሌ አጋማሽ 2016 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው አገር አቀፍ “የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ” መነሻ በማድረግ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሃሳባቸውን ያጋሩት በኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የሚንስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፤ “ኮዲንግ እና ኮደርስ” የሚሉትን ቃላት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ “ኮዲንግ እና ኮደርስ” የሚሉት ቃላት ከኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ ጋር ተያይዘው የመጡ ናቸው፡፡ ሠዎች ከኮምፒዩተር ጋር የሚነጋገሩበት ወይም የሚግባቡበት ቋንቋ የፕግራም ቋንቋ (Programming language) ይባላል፡፡ ብዙን ጊዜ ሠዎች “ኮዲንግ እና ኮደርስ” የሚሉትን ቃላት ፅንሰ ሃሳብ ከሚስጥር ጋር የሚያገናኙበት አረዳድ ስህተት ነው፡፡ ቃላቱ የኮምፒዩተር ተጠቃሚው ሠው እና ኮምፒዩተሩ ለተለያየ ዓላማ መግባባት የሚችሉበትን ሥርዓት ወይም አሠራር መፍጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡    ለምሳሌ፡- የተለያዩ ሶፍትዌሮች፣ መተግበሪያዎች፣ ፕላትፎርሞች እና መሰል የኮምፒዩተር መገልገያዎች ወደ አገልግሎት ከመግባታቸው በፊት ኮዶች ነበሩ። ኮዶቹን ተመራምረው እና ፈጥረው የሚፅፉ ሠዎች (ሙያተኞች) ኮደርስ ይባላሉ፡፡

ኮድ የማድረግ ተግባር በ21ኛው ክፍለ ዘመን አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው አገራት በዘርፉ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ቀን ከሌሊት የሚሠሩት። በዲጂታሉ ዓለም ላይ ያለውን ዕድገትና ፈጣን ለውጥ እያቀጣጠሉ ያሉት የአዳዲስ ሶፍትዌሮች፣ ገጸ ድሮች፣ መተግበሪያዎችን… ዕውን ማድረጊያ ቁልፉ በጥቂት ባለብሩህ አዕምሮ ግለሰቦች ዘንድ ይገኛል፡፡ ባለልዩ ተሰጥኦ ግለሰቦቹ የተሰወረውን ዕምቅ ብቃት መግለጥ የሚያስችላቸውን ምቹ ምህዳር ሲያገኙ፤ የዕውቀት ሻማቸውን ለብዙሃኑ ያበሩታል፡፡  

ኮድ የማድረግ ተግባር (Coding) ከሚያካትታቸው ዘርፎች መካከል፡- የገፀ ድር ልማት (web development)፣ የሶፍትዌር ልማት (software development)፣ የኮምፒዩተር ጨዋታዎች ልማት (game development)፣ ሣይንሳዊ የመረጃ ማጠናቀሪያና መተንተኛ (data science and analytics)፣ የሠው ሰራሽ አስተውሎትና የማሽን ትምህርት (artificial intelligence and machine learning) የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

  ከኮደሮቻቸው የተጠቀሙ አገራት

በዓለም ላይ የኮምፒዩተር ኮዲንግ የሚያወጡ ሙያተኞች (coders) ያላቸው አገራት ከሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል፤ እየተጠቀሙም ይገኛሉ፡፡ ዘርፉን በማልማትና በመጠቀም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል፡- አሜሪካ፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ እና ጀርመን ይጠቀሳሉ፡፡ ለአገራቱ ውጤታማነት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሊጋሯቸው የሚችሉ ቁልፍ ሥራዎችን በአግባቡ መከወናቸው ወሳኝ ሚና መጫወቱን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡  አገራቱ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋታቸው፣ ጠንካራ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች መገንባታቸው እና ዘርፉን የሚደግፍ የመንግስት ፖሊሲዎች መቅረፃቸው ከዘርፉ ቀዳሚ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡

እንደ ኤም አይ ቲ (MIT)፣ ስታንፎርድ እና ዩሲ በርክሌይ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ያሏት አሜሪካ፤ በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኮምፒዩተር ሳይንስ ምሩቃንን እንድታፈራ አግዟታል፡፡ ከእነዚህ ምሩቃን መካከል ለኮዲንግ ፈጠራ እና ልማት ልዩ ብቃት ያላቸውን ባለተሰጥኦዎች ተቀብለው የሚያሰለጥኑ ማዕከላት አሏት፡፡ እንደ ጀነራል አሰምብሊ (General Assembly) እና ፍላቲሮን ትምህርት ቤት (Flatiron School) ያሉ ተቋማት ደግሞ ባለልዩ ተሰጥኦ ወጣቶችን ተቀብሎ የማብቃትን ሚና ይወጣሉ፡፡

ሲሊከን ቫሊ፣ ሲያትል እና ኦስቲን በመሳሰሉ ከተሞች የገነቧቸው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መንደሮች ደግሞ ወጣቶቹ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር የሚለውጡባቸው ወሳኝ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የተቋማቱ በሥርዓት የተቃኘ፤ ጠንካራ ትስስር በመጨረሻ በጥራቱ እና በአገልግሎቱ ዓለም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችል የዲጅታል ቴክኖሎጂ ቁልፍ ግብዓት ባልተቋረጠ መልኩ እንዲያወጡ አስችሏቸዋል፡፡

አሜሪካ ከዘርፉ እያገኘች ያለው ጥቅም፤ ፍሬውን ለመብላት የሚያስፈልገውን የጥረት መጠን ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ይህንን በተመለከተ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2021 በCompTIA Cyberstates 2021 የተሰኘ ገፀ-ድር ይፋ የሆነ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አገሪቷ በተጠቀሰው ዓመት ብቻ ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ ከ12 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥራበታለች። ከአገር ውስጥ ምርቷ የ10 በመቶ ድርሻንም መያዝ ችሏል፡፡ 

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የምህንድስና ተማሪዎችን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማቷ የምታስመርቀው ሕንድ፤ የዘመናችን ቁልፍ መሣሪያ በሆነው ኮዲንግ (Coding) አማካኝነት የተለያዩ ጥቅሞችን በማግኘት ላይ ነች፡፡ የህንድ የቴክኖሎጂ ተቋም (Indian Institutes of Technology- IITs) እና ሌሎች የምህንድስና ኮሌጆች የአገሪቷን ወጣቶች መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት የማስታጠቅ ሚናቸውን ይወጣሉ፡፡ ከወጣቶቹ መካከል የተሻሉት ተመርጠው ስኪል ኢንዲያ (Skill India) እና ናስኮም ፊውቸር ስኪል (NASSCOM Future Skills) ዓይነት የመንግስት እና የግል የቴክኖሎጂ ተቋማት በመግባት ክህሎታቸውን ወይም ውጥኖቻቸውን ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚለውጡበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። በዚህ መንገድ ያለፉት የሕንድ ሙያተኞች በዕውቀታቸው፣ ክህሎታቸው እና መሬት በነካው ውጤታማነታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ከተሰጣቸው ውሎ አድሯል፡፡ ለዚህ ምስክሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት ከኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው መስኮች ተቀጥረው እየሠሩ ያሉ ሕንዳውያን ቁጥር ቀላል የማይባል መሆኑ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን (አይቲ) እና የሶፍትዌር አገልግሎት ኢንዱስትሪ ለሕንድ የወጪ ንግድ ገቢ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው እና በዓመት እስከ 150 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2022 የወጣው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ ይጠቁማል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፤ ሕንድ ዘርፉን ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ቀጥሮ ማሠራት የሚችልበት ደረጃ ላይ አድርሳዋለች። ይህም በዓለም ላይ ካሉት ትልቁ የቴክኖሎጂ የሰው ኃይል አንዱ ያደርጋታል። ዘርፉን የበለጠ ለማሻሻልና ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የሠው ኃይል ልማት ላይ አተኩራለች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት (2022) በዓመት ቁጥራቸው ከ400 ሚሊዮን በላይ ነባር እና አዳዲስ ሙያተኞችን  ለማሰልጠን ያለመ መርሃ ግብር በመንግስት ደረጃ ይፋ መደረጉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ 

አሊባባ (Alibaba)፣ ቴንሰንት (Tencent)  እና ሁዋዌ (Huawei) የመሳሰሉ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤቷ ቻይና፤ በዘርፉ ያላትን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በተቋማት ግንባታ እና ብቁ ትውልድ በማፍራት ላይ አተኩራ ትሠራለች፡፡ ዘርፉ በመንግስት እንደ ዓይን ብሌን ይቆጠራል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከላት፣ የግል ኩባንያዎች በተናበበ መንገድ ተቀናጅተው ሚናቸውን ይወጣሉ፡፡ በአይሲቲ ልማት ላይ ቁልፍ አስተዋፅኦ ያለውን የኮዲንግ እና ተዛማጅ ዕውቀትና ክህሎትን የጨበጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን ወጣቶች በባትሪ ተፈልገው ወደ ሥራ የሚገቡበት ወሳኝ የሥራ መስክ  ተፈጥሯል፡፡ ሙያተኞቹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence-AI)፣ በ5ኛ ትውልድ (5 Generation- 5G) እና በኤሌክትሮኒክስ ግብይት (e-commerce) በመሳሰሉት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ወሳኝ መገልገያ መሣሪያዎች ልማት ላይ በውጤታማ ተሳትፏቸው ቀጥለውበታል፡፡ ቻይና ከዲጂታል ኢኮኖሚው ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ እና ከጥቅል አገራዊ ምርቷ ያለው ድርሻ ወደ 38 ከመቶ ከፍ እንዲል የማስቻሏ ምስጢሩ ሥራና ሥራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጅምር

“ከቀረ የዘገየ ይሻላል” የሚለው ተደጋግሞ የሚነገር ነው፡፡  የውድድር ሜዳው ለሁሉም እኩል ዕድልን ይዞ በመጣበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአባባሉ ትርጉም ውሃ አያነሳም። ምክንያቱም በዚህ ዘመን መዘግየት ከመቅረት አይተናነስም። ፈጣን እና ተለዋዋጭ ሁነት በበዛበት የዓለም ሁኔታ ውስጥ በመዘግየት የሚፈጠረው ጉድለት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ ነባራዊውን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ አካሄድን ማስተካከል ይጠበቃል፡፡ ይህ ደግሞ ከግለሰብ እስከ አገር ድረስ ይዘልቃል፡፡

በዲጂታሉ ዘርፍ የኢትዮጵያ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በጅምር ያለ ስለመሆኑ በኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ይስማማሉ። እሳቸው እንደሚያብራሩት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታሉ መስክ ያላትን ተሳትፎ ከተመለከትን በአንጻራዊነት ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ ይህንን ጉድለት ለመሙላት አገራችን ወደዲጂታል ኢኮኖሚ እየገባች ትገኛለች። ዲጂታል ኢኮኖሚ ደግሞ ያለዲጂታል ክህሎት አይሳካም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ከዲጂታል ኢትዮጵያ ዓላማ ጋር አብሮ ለመጓዝ ክህሎታቸውንም ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ለኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሙያተኞች ብቻ ሳይሆን ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። አገልግሎትን በዲጂታል ለመስጠትም ሆነ ለመገልገል ክህሎቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን እያንዳንዱ መገልገያ ዲጂታል እየሆነ ነው፡፡ እንደ ልብስ ማጠቢያ፣ ቤት ማፅጃ እና መሰል የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ጨምሮ፣ የቢሮ መገልገያዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች፣ የገንዘብ ዝውውሮች… ዲጂታል በሆነ አሠራር የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን አገልግሎቶች በሚገባ ለማግኘት ዲጂታል ክህሎት አስፈላጊነቱ የግድ ይሆናል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ይፋ የሆነው “የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ” ከነባራዊው ዓለም ጋር አብሮ የመጓዝን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳይንስ ሙዚየም ኢንሼቲቩን ባስጀመሩበት ወቅት፤ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በተያያዥ የዲጂታላዜሽን ክህሎቶች የሚሰለጥኑበት፣ ዘመኑን በዋጀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ዕድልን ይዞ የመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ የነገ ተስፋዎች የሆኑ ወጣቶች ስልጠናውን በጥሞና በመከታተል ስራ ፈጣሪ፣ ኩባንያ ፈጣሪና በዓለም ገበያ ተወዳድረው ለመቀጠር እና ለኢትዮጵያ የነገ ተስፋ ለመሆን ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለምን በተቆጣጠረበት በዚህ ዘመን፤ ጊዜው የሚጠይቀውን አቅምና ብቃት ይዞ መገኘት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ክህሎት በጣም ወሳኝ ነው። እንደ አገር ይፋ የተደረገው ኢንሼቲቭም ዋና ዓላማው የዲጂታል ክህሎታቸው የዳበረ ወጣቶችን ማፍራት ሲሆን፤ በተጨማሪም የተለያዩ ተጠባቂ ውጤቶችን ማሳካት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አብዮት (ዶ/ር)፤ የኮዲንግ ክህሎት አንዱ የዲጂታል ክህሎት አካል ሲሆን፤ ከሌሎች ክህሎቶች አንፃር የረቀቀ እና ትልቅ አቅም ይጠይቃል። የኮዲንግ ክህሎትን ለማሳደግ እና ለመጠቀም የዲጂታል ክህሎት መሰረታዊ ነው፡፡ የዲጂታል ክህሎት ያላቸው ሠዎች ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት እንዲሁም አዳዲስ የፈጠራ አቅማቸውን የሚያወጡበት ሁኔታ ሲመቻችላቸው ኮዶችን ወደ መፍጠር ይገባሉ። በቅረቡ ይፋ የተደረገው “የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ” ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ያላቸውን ዕምቅ አቅም የሚጠቀሙበትን መልካም ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም የተሻለ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞን ስኬታማነት ለማገዝ እና በዘርፉ የአገሪቷን ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተስፋ በተጣለበት በዚህ ኢንሼቲቭ ላይ ለመሳተፍ ማሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶች፣ ስለአገልግሎቱ እና ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ አስመልክቶ አቢዮት (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤   ኢንሼቲቩን መሰረት ያደረገው ትምህርትና ስልጠና የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካለው ‘ዩዳሲቲ’ (UDACITY) በሚባል ፕላትፎርም አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ፕላትፎርም በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርቱን ያሟሉ እና ተወዳዳሪ የሆኑ ሙያተኞችን ማፍራት የሚያስችለውን የትምህርትና ሥልጠና ስርዓተ ትምህርት (ካሪክለም)፣ ኮርሶች፣ የምዘና ሂደቶች … ይጠቀማል፡፡ ሥልጠናው ላይ ከዚህ በፊት በሙያው ላይ ያሉ ወይም ለሙያው አዲስ የሆኑ ፍላጎቱ ያላቸውና ፕላትፎርሙ የሚጠይቀውን መስፈርት የሚያሟሉ ኢትዮጵያውያን መውሰድ ይችላሉ፡፡ ሥልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ያጠናቀቁ እና ምዘናውን ያለፉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) ያገኛሉ፡፡ አሁን ላይ እየተስፋፋ በመጣው የኦንላይን ሥራ ላይ ለመቀጠር ይህንን ሂደት ማለፍ ወሳኝነት አለው፡፡

አክለው እንዳብራሩትም፤ ይህንን ኢንሼቲቭ በአግባቡ መጠቀም እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሙያተኞችን ማፍራት ከተቻለ ዘርፈ ብዙ ውጤት ማሳካት ይቻላል፡፡ በመጀሪያ ደረጃ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በአገር ውስጥም በውጪ አገራትም ተቀጥረው መሥራት ይችላሉ፡፡ የራሳቸውን የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በሂደትም ብዙ ዜጎችን መቅጠር የሚችል ኩባንያ እስከ መመስረት የሚደርሱም ይኖራሉ። እንደአገር ከውጭ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ምርቶችንና መተግበሪያዎችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ይቻላል። በሁለተኛነት ደግሞ፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅምን ያሳድጋል። ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አንድ አገር ሄደው መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ፤ ቀድመው ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ ‘በዚያች አገር ምን ያክል በዲጂታሉ ዘርፍ በዕውቀትና በክህሎት የበቃ የሠው ኃይል አለ?’ የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ኢንሼቲቩ ኢትዮጵያ በቀጣይ ተመራጭ አገር እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር የሚከውነው ይህ ኢንሽቲቭ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት  ውስጥ 5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ኮደሮችን የመፍጠር ግብ አስቀምጧል፡፡ ለሥራው ስኬታማነት ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ከቻለ ዕቅዱ ከዚህም በላይ ማሳካት እንደሚቻል ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “ከበረታን እስከ 7 ሚሊዮን ማድረስ እንችላለን” በማለት ነበር የገለፁት፡፡ የወጣቶች አገር የሆነችው፣ ከወጣቶቿም አብዛኞቹን ያስተማረችው ኢትዮጵያ ለዘርፉ ማደግ ወሳኝ አቅም የሆነውን የሞባይል ስልክ የሚጠቀም ሕዝቧ ቁጥር ከ85 ሚሊዮን በላይ መድረሱ፣ ከዚህም ውስጥ 45 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘቱ እንደ መልካም ዕድል የሚወሰድ ነው፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review