AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የቦሌ አራብሳ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል ፡፡
ከለዉጡ ወዲህ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ጀምሮ የመጨረሶ አንዱ ማሳያ የሆነዉ ይህ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የከተማችንን የፍሳሽ ማጣራት አቅም ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት በቀን 48 ሺሕ ሜትር ኪዮብ ወደ በቀን233 ሺሕ ሜትር ኪዮብ ከፍ ማድረግ መቻሉንም አመልክተዋል::
ይህ የቦሌ አራብሳ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ከ240 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናዊ ፍሳሽ ማጣሪያ ፣ስርዓት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነዉ።
ለአንድ ከተማ ወሳኝ ከሆኑ መሰረተ ልማቶች መካከል የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓትን ማዘመን ትልቅ ስራ ሲሆን ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነውም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ የፍሳሽ ማጣሪያ ስራ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓታችንን የሚያዘምን፣ የከተማችን ነዋሪዎችን እና በአጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎት የረዥም ጊዜ ቅሬታን ምላሽ የሚሰጥ ፣ከተማችንን ከብክለት የጸዳች፣ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የጀመርነውን ስራ እዉንየሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከተማችን አዲስ አበባን ጽዱ፣ ውብ እና የመኖሪያና ስራ ተስማሚ ከተማ፣ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሁም የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ለዘመናዊ ከተማ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በውጤት እያጠናቀቅን ነዉ ሲሉም ነው ከንቲባዋ መልእክታቸውን ያስተላለፉት።