AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
የተሀድሶ ስልጠናው ወደማህበረሰቡ ሲመለሱ የልማትና የሰላም አካል የሚሆኑበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች ገለጹ።
የፌዴራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ዓለማቀፋዊ ተቋማት በተገኙበት በመጀመሪያ ምዕራፍ 75ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ስልጠና በዘላቂነት የማቋቋም ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት በመቀሌ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
በዚህም በመቀሌ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከል የገቡ 320 የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ የዘላቂ ማቋቋሚያ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደየመጡበት አካባቢ ተመልሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም በዕዳጋ-ሀሙስ እና መቀሌ የተሀድሶ ስልጠና ማዕከላት 640 የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ስልጠናውን በመከታታል ላይ ካሉ የቀድሞ የክልሉ ታጣቂዎች መካከል ፍፁም አፅብሀ፥ በጦርነት ወቅት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማቋረጥ አስከፊ ውጣ ውረድ ማሳለፉን አስታውሷል።
በዚህ መደገም በሌለበት ትርጉም አልባ የጦርነት ውጣ ውረድ ታልፎ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ለስልጠና መብቃቱ ደስታ እንደፈጠረለት ተናግሯል።
ሌላኛዋ የቀድሞ የክልሉ ታጣቂ መድኅን ገብረ-መስቀል ፤ በርካቶችን ለህልፈትና ለንብረትንም ውድመት በተዳረጉበት የጦርነት ወቅት በተለይም ለሴቶች ፈታኝ እንደነበረ ታስታውሳለች።
የመቀሌ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከል ተጠቃሚ ገብረ-ሕይወት ገብረ-ሚካኤልም እንዲሁ፤በጦርነቱ ወቅት ከነበረው ርሀብና የውሃ ጥም በተጨማሪ የምንወዳቸውን ጓደኞቻችን ማጣታችን የጦርነትን አላስፈላጊነት የሚያሳዩ ናቸው ብሏል።
ያ ሁሉ ታልፎ በማዕከሉ የሚሰጣቸው ስልጠና በጦርነት ወቅት የደረሰባቸውን የሥነ-ልቦና ጫና በማስወገድ ቀጣይ ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግሯል።
በጦርነት የሚፈታ ነገር ባለመኖሩ ከዚህ ጥፋት ትምህርት መውሰድ ይገባል ያለችው ደግሞ የቀድሞዋ ታጣቂ ዝናብ ጨርቆስ ነች።
ሰላምን አጽንቶ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁማ፤ በማዕከሉ የሚሰጣቸው ትምህርትና ስልጠናም ወደማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸውን አስተካክሎ ለመምራት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፃለች።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ የሚሰጣቸው የዘላቂ ማቋቋም የተሀድሶ ስልጠናም ወደማህበረሰቡ ሲመለሱ የልማትና የሰላም አካል የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።
በስልጠናው መሰረትም በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በየአካባቢያቸው በመሄድ በግልም ሆነ በማኅበር በመደራጀት የተሻለ የልማት ስኬት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአንድ አንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችንም በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ በመስጠት ለሀገር ዕድገት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቀጣይም አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ የሀገር የልማት አካል በመሆን ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ፤በፌደራል መንግስት፣በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ተባባሪ አካላት ትብብር የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በየአካባቢያቸው ከሄዱ በኋላም በዘላቂነት ለማቋቋም ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞ ታጣቂዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ የሀገርና የክልሉ የልማትና የሰላም አካል እንዲሆኑ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በቀዳሚነት እየሰራ እንደሚገኝ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።