የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ስኬት አምጥቷል – አቶ ማሞ ምህረቱ

You are currently viewing የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ስኬት አምጥቷል – አቶ ማሞ ምህረቱ

AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥና ተጨባጭ ስኬት ማምጣቱን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

አቶ ማሞ ምህረቱ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ከተከናወኑ ትላልቅ የሪፎርም ስራዎች መካከል በተለይም በኢኮኖሚ ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ታሪካዊና ድፍረት የተሞላበት መሆኑን አስታውሰው በዚህም በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን መቋቋም በሚያስችል መልኩ የተከናወነና ውጤቱም የተሳካ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

ከገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያው በፊት የምርትና ምርታማነት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት ሀገሪቱን ሲፈትናት እንደነበር አስታውሰው ከማሻሻያው በኋላ ግን የዋጋ ንረቱ ከነበረበት 30 በመቶ አሁን ላይ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ የተደረገው ማሻሻያ በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነትን በሚፈለገው ልክ ለማስተካከል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን በየጊዜው ሲፈትናት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሰረታዊ በሚባል መልኩ ያቃለለ ከመሆኑም ባለፈ የውጪ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችቱ ከ200 ፐርሰንት በላይ ከፍ እንዲል ማድረጉን ገልጸዋል።

የውጪ ምንዛሬ ግኝቱ መስፋት ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በሚሰበስበው ቁጠባና በሚያበድረው ብድር በየዓመቱ ከ25 በመቶ በላይ ዕድገት የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የታክስ አሰባሰቡ እያደገ መምጣቱንና የመንግስት የውጭ ዕዳዎች እየተቃለሉ መምጣታቸውንም ነው አቶ ማሞ ያብራሩት።

የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎቹ የተቀናጁና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርጉ በመሆናቸው በተለይም የኤክስፖርት ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እያበረታቱ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review