AMM-ታህሣሥ 26/2017 ዓ.ም
የተሰረቁ ስልኮችን እንደሚገዛ የተጠረጠረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ ።
ከህብረተሰቡ በመጣ ጥቆማ ህጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ የተሰረቁ ሞባይል ስልኮችን ይገዛል በሚል የተጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር በማዋል ተገቢውን ምርመራ እያጣራ መሆኑን የጉለሌ ክ/ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል ።
ታህሳስ 8 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 9:00 ሠዓት በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አስኮ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ፖሊስ ከህብረተሰቡ የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግና ተገቢውን የፍርድ ቤት የመያዣና የብርበራ ትዕዛዝ በማውጣት በተጠርጣሪው ሞባይል ጥገና ሱቅ ውስጥ ባደረገው ብርበራ የተለያየ ሞዴል ያላቸውን 30 ተቀሳቃሽ ስልኮችን እና ሁለት ታብሌቶችን ከነተጠርጣሪው ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ መገለጹን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
ተመሳሳይ ወንጀል ተፈጽሞብኛል የሚል ካለ አስኮ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል በመቅረብ የተሠረቀበትን ስልክ መለየትና መረከብ የሚቻል ሆኖ ህብረተሰቡ መሠል የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል በተለያዩ መንገድ የተሰረቁ ንብረቶችን ባለመግዛት ፖሊስ እየሰራ ያለውን የወንጀል መከላከል ስራ ማገዝ እንደሚኖርበትም የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን ያስተላልፋል።