የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ስርቆት

You are currently viewing የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ስርቆት

ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን በመስረቅ እና በመሸሸግ ወንጀል የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN- ሀምሌ 4/2016 ዓ.ም

አንድ ከባድ ተሽከርካሪን ጨምሮ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን በመስረቅ እና በመሸሸግ ወንጀል የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች ከነንብረቱ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ሰኔ 7 ቀን 2016 ከለሊቱ 6 ሰዓት ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ቁስቋም ማርያም አካባቢ ነው ።

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የሰርቲ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል ምርመራ ቲም ሀላፊ ዋና ሳጅን አለቤ ባልኬ እንደተናገሩት አቶ በሪሁን ረጋሳ የተባሉት የግል ተበዳይ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-69135 ኢት የሆነ ተሽከርካሪያቸውን በራሳቸው ጋራዥ ውስጥ አቁመው በነበረበት አጋጣሚ ነው ወንጀሉ የተፈፀመው፡፡

የደረቅ ጭነት ማመላለሻ የሆነውና 4 ሚሊዮን ብር የዋጋ ግምት ያለው አይቪኮ ትራከር ጋራዡ ውስጥ ቆሞ በነበረበት ወቅት የጋራዡ አንድ የጥበቃ ሰራተኛ ከሌሎች አራት ግብራበሮቹ ጋር በመመሳጠር ተሽከርካሪውን ሰርቀው መውሰዳቸውን ዋና ሳጅን አለቤ ተናግረዋል፡፡

የግል ተበዳይ አቶ በሪሁን ረጋሳ የተሽከርካሪ ጥገና የሚከናወንበት ጋራዣቸውን የቦታ ለውጥ ለማድረግ በሂደት ላይ የነበሩ ሲሆን በዚሁ ሂደት ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ በከባድ ተሽከርካሪያቸው ላይ ጭነዋቸው የነበሩ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች አብረው መወሰዳቸውን የምርመራ ቲም ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ የግል ተበዳይን አቤቱታ ተቀብሎ ባደረገው ክትትል የጥበቃ ሰራተኛውን እና አራቱ ግብራበሮቹን በሸገር ከተማ ኮዬ ንፋስ ስልክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መኪናውን ለመሸጥ ሲደራደሩ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማጣራት በአቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸዋል ፡፡

በተሽከርካሪዉ ላይ ተጭነው የነበሩት የተለያዩ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ብረታ ብረት ለሚገዙ ግለሰቦች በኪሎ ተሽጠው እንደነበር የሚናገሩት ዋና ሳጅን አለቤ፤ ንብረቶቹን የገዙ እና የሸሸጉ 13 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋልና የተሸጡትን ዕቃዎች በማስመለስ ምርመራ እያጣራን እንገኛለን ብለዋል።

የጥበቃ ሰራተኞችን የሚቀጥሩ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፖሊስ ተደጋጋሚ መልዕክቶችን እያስተላለፈ እንደሚገኝ ያስታወሱት ዋና ሳጅኑ፤ አሁንም ቢሆን ለንብረቶቻቸው ተገቢውን ትኩረት የመስጠት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

#Addisababa

#Ethiopia

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review