የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ዜጎች 85 ቶን ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን አደረገ
AMN-ሐምሌ 20/2016 ዓ.ም
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ዜጎች 85 ቶን ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን መላኩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።
በስፍራው በደረሰው አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እስካሁን 60 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በገንዘብ እና በቁሳቁስ መልክ መደረጉም ተገልጿል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግስት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ዜጎች 85 ቶን ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን መላኩ የተገለፀ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ሀገራት እና ተቋማትም አደጋውን ተከትሎ አጋርነታቸውን እየገለፁ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በአካባቢው ተጨማሪ አደጋ እንዳያጋጥምም ወደ ስፍራው ባለሙያዎችን በማሰማራት የአየር ሁኔታ እና የከርሰ ምድር ጥናት እየተካሄደ ስለመሆኑም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገልፀዋል።
በአደጋው የጠፉ ዜጎችን የማፈላለግ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትር ዴኤታዋ ከአደጋው የተረፉ ዜጎችንም ወደ አራት የተለያዩ አካባቢዎች ለማስፈር እየተሰራ ነውም ብለዋል።
አደጋውን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቅዳሜ ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት ብሄራዊ ሀዘን ማወጁም ይታወቃል።