“በአንድ አጋጣሚ አንድ አሜሪካዊ ቢሊየነር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ውስጥ መኪኖች ያሉበትን ቦታ አሳይቼው ነበር፡፡ ከመኪናዎቹ አንዱን ከተመለከተ በኋላ ‘ይህንን መኪና አውቀዋለሁ፤ አያቴ ነበራቸው። …በህጻንነቴም እየተጫወትኩ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍም አለኝ በማለት መኪናው ቆሽሾ በማየቱ ተገረመ::” ይላሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከአራት ዓመት በፊት በሀገር ውስጥ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተላለፈውና ብሔራዊ ቤተ መንግስቱንና ቅርሶቹን እያስጎበኙ በተናገሩበት “የኢትዮጵያ ልክ፤ ከግቢ እስከ ሀገር – የእዩቤልዩ ቤተ መንግስት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ላይ፡፡ “አሜሪካዊው ቢሊየነር እንጦጦ እና አንድነት ፓርክን ጨምሮ ከተመለከተና ህልሜን ካጋራሁት በኋላ ‘አግዘኝ’ ስለው ግን ‘አዝናለሁ፤ አላግዝህም’ ነው ያለኝ፡፡ ‘ያለውን አቧራ አልብሶ የደበቀ፣ ብታግዘውም የሰጠኸውን ከማበላሸት ውጪ ሊያሳምረው አይችልም፡፡… መጀመሪያ ያላችሁን ሀብት አውቃችሁ ብታወጡት፤ እሱ ላይ መጨመሩና ማገዝ ይቀላል፡፡ ይህን የሚያክል መሬት፣ ሊሸጥ የሚችል ታሪክ ይዛችሁ መጠቀም ያልቻላችሁ ብትታገዙም ብዙ ለውጥ ላታመጡ ትችላላችሁ’ አለኝ፡፡ በወቅቱ ይህ ሰው ተሰምቶት ያደረገው ንግግር፣ ያለንን ሀብት አለመጠቀም ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ እንድገነዘብ ዕድል ሰጠኝ” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡
በተለያዩ መንግስታት ብዙ የታሪክ ክስተቶችን ያስተናገደው፣ በኪነ ሕንፃ ውበቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ በያዛቸው ቅርሶችና ሀብቶች ልዩ የሆነው ብሔራዊ ቤተ መንግስት ለሦስት ዓመታት ያህል እድሳት ሲደረግለት ቆይቶ ከሰሞኑ ለጉብኝት ክፍት ሆኗል፡፡
የአፄ ኃይለሥላሴን 25ኛ ዓመት (የብር እዩቤልዩ) የንግሥና ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የተገነባው ቤተ መንግስቱ በንጉሱ ዘመን “እዩቤልዩ ቤተ መንግስት” ይባል ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ “ብሔራዊ ቤተ መንግሥት” በሚል ስያሜ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም አሁን አንድነት ፓርክ ከሆነው የታላቁ ቤተ መንግስት ጋር በማነፃፀርም “የታችኛው ቤተ መንግሥት”ም ይባል ነበር።
በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የርዕሰ ብሔሮች መኖሪያና እንግዳ መቀበያ፤ ሀገራዊ የክብር ክዋኔዎች ማስተናገጃ በመሆን አገልግሏል፡፡ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች፣ ሪቻርድ ኒክሰን፣ ጆሴፍ ቲቶ፣ የግሪኩ ንጉስ ጳውሎስ፣ የዮርዳኖሱ ንጉስ ሁሴን፣ ባራክ ኦባማን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተመላልሰውበታል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ቤተ መንግሥቱ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ የኪነ ሕንፃ እሴት እና የዘመናዊ ኪነ ህንፃ ለዛ አጣምሮ የያዘ እንደሆነ ይነገርለታል። በትላልቅ ዛፎች ውብ ገጽታ የተላበሰ፤ ድንቅና ብርቅ ታሪካዊ ሀብቶች ይገኙበታል።
ሙዚየም፣ ዘውዶች፣ ዙፋኖች፣ በቆዳ የተለበጡ መጻሕፍት፣ ከዓለም ዙሪያ ለኢትዮጵያ መንግስት የተበረከቱ ስጦታዎች፣ የተለያዩ የሀገራት መሪዎች ፎቶ ግራፎች፣ ቅርጻ ቅርጾች፣ የመመገቢያ ዕቃዎች፣ የተለያዩ የሥነጥበብና እደ ጥበብ ውጤቶች፣ ዘመናዊ ካፌና ሬስቶራንቶች፣ … በቤተ መንግስቱ ከሚገኙ ሀብቶች ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
የቤተ- መንግስቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ
የኢትዮጵያ የባህልና ቅርስ ሀብት መድብል የሆነው ብሔራዊ ቤተ መንግስት በሚያምር መልኩ ታድሶ ለእይታ ክፍት መሆኑ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ቤተ መንግስቱ በተመረቀበት ወቅት፣ “ዳግመኛ የተወለደው ይህ ቤተ መንግስት ለታሪካችን ድንቅ ምስክር ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ የቱሪስት መስህብ፣ የዲፕሎማሲ ተግባራት መከወኛ፣ የባህል ልውውጥ ማዕከል፣ የውይይትና የትብብር መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል አምናለሁ። መጪው ትውልድ ከቀደሙት ሰዎች ውርስ ጋር የሚገናኝበት የታሪክ ሀብልና ሰንሰለት ይሆናል፡፡” ሲሉ ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ ልክ፤ ከግቢ እስከ ሀገር” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ጥናታዊ ፊልም ላይ እንዲህ ዓይነት የተደበቁ፣ ለሀገር ብዙ ጥቅም ማምጣት የሚችሉ የታሪክ ሀብቶችን ማውጣት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ የአንድነት ፓርክን በተመለከተ ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት ይቻላል፡፡
“ኢትዮጵያ የሆኑ ሰዎች የጀመሯት የሆነ ቦታ የምታበቃ አይደለችም፡፡ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ መሪዎች ስማቸው፣ ግብራቸው፣ አመጣጣቸው፣ ቋንቋቸው ቢለያይ የኢትዮጵያ መሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ለእያንዳንዱ የምንሰጠው የሚያማምሩ ታሪኮችና ጥፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከጥፋቶቻቸው፣ ከመልካም ስራዎቻቸው እንማራለን። የተሻለ ነገር እያደረግን እንሄዳለን። የትናንትናን ‘አላውቅህም’፤ ‘አላየሁም’ ማለት አያዋጣም። … ያ ታሪክ እንደገና እንዲቀመጥ የተደረገው ከትናትና መማር ስላለብን ነው፡፡ ከትናንት ያልተማረ ነገን መስራት ስለሚቸገር፡፡” ብለዋል፡፡
የጋራ ትርክት ሰበዝ
በሶማሊላንድ ሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩትና የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር አቶ በፈቃዱ ዳባ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስት የኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ታሪክ አቅፎ የያዘ፣ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች የተከወኑበት፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ከተለያዩ ሀገራት ጋር ውይይት ያደረጉበት ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡ እንደ ህዝብና ሀገር ልንኮራበት የሚገባው በአፍሪካና በዓለም ላይ በጎ ተፅዕኖ የፈጠርንበት ስፍራ ነው፡፡
አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ቁልፍ ሚና የተጫወተችበት፣ ከራሷ አልፋ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻለችበት፣ ሀገረ መንግስቷ የተጠናከረበት፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል ስትሆን በርካታ ስራዎች የተሰሩት በዚህ ቦታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ታሪክ ልዩ ቦታ ያለው ቤተ መንግስቱ ታድሶ ለህዝብ ክፍት መደረጉ ትውልዱ ከቆየ የመንግስትነት ልምድ እንዲማርና በታሪኩ እንዲኮራ የሚያደርግ ስራ መሆኑን አቶ በፈቃዱ ይናገራሉ፡፡ ትውልዱ በቤተ መንግስቱ ያሉ ሀብቶችን በመመልከት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ምን መልክና አሻራ ጥሎ እንዳለፈ የሚረዳበትና ራሱን የሚፈትሽበት፣ አሁን ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ፣ መስተካከል ያለበትን እያስተካከለ ጠንካራ ሀገር እንዲገነባ መማማሪያ መድረክ ይሆናል። ቤተ መንግስቱም ታድሶ የቱሪዝም መስህብና የትውልድ መነጋገሪያ፣ መማሪያ መድረክ እንዲሆን መደረጉ የጋራ ትርክት ለመገንባት እና በብዙ መልክ ወደ አንድነት ለመምጣት እድል ይፈጥራል፡፡
“ወደድንም ጠላንም ታሪኮቻችን የትውልድ አሻራ ውጤቶች ናቸው። ታሪኮቻችንና ቅርሶቻችን ተሸፋፍነው ከሚቀመጡ፣ በቅርስነታቸው ተጠብቀው ትውልዱ አይቶ እንዲያደንቅ፤ የሚተቸውም ከሆነ እንዲተቸው፣ ሀገርና ዓለም እንዲያውቀው፣ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ለጉብኝት ክፍት መደረጉ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ያስረዳሉ፡፡
ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራት ከጀመሩ ወዲህ የተደበቁ የባህልና ታሪክ ሀብቶችን በማውጣትና አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን በመገንባት ኢኮኖሚውን እንዲደግፉና ትውልድ እንዲማርባቸው እየሰሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሙሉዓለም ኃ/ማርያም ናቸው፡፡
ያለፍንባቸው መንገዶች የታሪካችን አካል ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቱን የመሩ መሪዎች ከነጥንካሬና ድክመቶቻቸው ሀገርን መምራታቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ታሪክ የሚያስፈልገው ካለፈው ትምህርት ለመውሰድ ነው፡፡ ብሔራዊ ቤተ መንግስት በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች ታላላቅ ሀገራዊ ኩነቶችን ሲያስተናግድ የቆየ ስፍራ እንደመሆኑ ታድሶ ለእይታ ክፍት መሆኑ እንደ ሀገር የጋራ ትርክት ለመገንባት ጠቃሚ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የብሔራዊ ቤተ መንግስት እድሳት የጋራ ትርክት ግንባታ አንዱ አካል እንደሆነ አስረድተዋል። የጋራ ወይም አሰባሳቢ ትርክት ሀይል የሚያሰባስብና ጠንካራ ሀገርን ለመፍጠር መሰረት የሚሆን ነው፡፡ የመደመር መንገድ የትናንት ጠቃሚ ወረቶችን፣ ከዛሬና ነገ ጋር አስተሳስሮ መጠቀም ማለት ነው፡፡
ቤተ መንግስቱ ባለፉት ሀምሳ ዓመታት እንደ “የፊውዳል ቤት” ተቆጥሮ ተረስቶ የቆየ ስፍራ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እድሳት ባይደረግለት በውሃ ተቦርቡሮ ሊፈርስ ይችል ነበር፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በታሪክ መዝገብ ማቆየት ብቻ ሳይሆን ብዙ ገንዘብ ማግኘት በሚያስችል መልኩ ተውቦ እንዲሰራ መደረጉንና ከትናንት የተገኘውን ጠቃሚ ነገር ከዛሬ በማስተሳሰር የጋራ ትርክት ለመገንባት የሚሰራው ስራ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ ምን ይጠበቃል?
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ በፈቃዱ እንደሚናገሩት፣ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የተለያዩ ትርክቶችን ማስታረቅ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ በጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ትርክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ትርክቶች ቀጣይነት እንዳይኖራቸው ህዝብ እንዲነጋገር እና የመደማመጥ ባህል እንዲያድግ መስራት ያስፈልጋል። አንዱ ሌላውን በማግለል፣ በጥላቻ የተቀየረና ወደፊት የሄደ ሀገር የለም። በታሪክ አጋጣሚ አብረን የተሳሰርን ማህበረሰብ እንደመሆናችን በሀገር አቀፍም ይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ጥሩ የሆኑ ታሪኮች ማውጣት፤ በልዩነቶች ላይ ደግሞ በመነጋገር የተሻለ ሀገር ለመፍጠር መስራት ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት ከአሰባሳቢ ይልቅ ለነጠላ ትርክት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር የሚያነሱት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ ያ መንገድ እርስ በርስ መከፋፈልን፣ ቅራኔን፣ በሊሂቃን መካከል ያለመተማመንን በማስፋት የሀገር ግንባታው እንቅፋት ነው የሆነው። እንደ ሀገር በቅርብ ጊዜ ያጋጠሙ አለመግባባቶችና ግጭቶች አንዱ ምክንያትም ከዚህ የመነጨ ነው። በቀጣይም ልክ እንደዚህ ዓይነት የተረሱ ሀብቶችን በማውጣት የኢኮኖሚ ማነቃቂያ፣ የትውልድ መማሪያና የወል ትርክት መገንቢያ መሳሪያ እያደረጉ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ