AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም
የተፋሰስ ልማታችንን በማስፋት የአፈር ሀብታችንን ለብልጽግናችን ለማዋል መረባረብ ይገባናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩን በዛሬው ዕለት ማብሰራቸውን ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ግብን ለማሳካት በየዓመቱ ከ14 ሚልዮን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ መጠነ ሰፊ የተፋሰስ ልማት ተግባራትን በማከናወን እመርታዊ ለውጥ መጥቷልም ነው ያሉት።

የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብትና የተፋሰስ ልማትን በመተግበራችንም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ቁርጠኝነታችንን አሳይተናል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎች አገግመዋል፣ የአፈር መከላት ቀንሷል፤ የደን ሽፋን ወደ 23.6 በመቶ አድጓል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማቶችን በመጠበቅና በባለቤትነት በመያዝ የንብ ማነብ፣ የእንስሳት ርባታ፣ የመስኖ ልማት እና የፍራፍሬ ልማትን በመተግበር ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ እስካሁን ያስመዘገበችው ስኬት በመንግሥት አመራር፣ በሞያተኞች በኅብረተሰቡና በልማት አጋሮች ተሳትፎ የተገኘ ድምር ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ዓመት በ4 ነጥብ አንድ ሚልዮን ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት በማሳካት ሁሉም አካላት በትጋት እንዲረባረቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

All reactions:
31Abate Feyissa and 30 others