“የቱሪዝም ባለሙያ መሆን ኢትዮጵያን በተጨባጭ ለማወቅ እድል ይፈጥራል”-የጂኦቱሪዝም ባለሙያው እንቁ ሙሉጌታ
አቶ እንቁ ሙሉጌታ ይባላሉ:: ኢትዮጵያ መልከ ብዙ፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት፣ የቅርስና የባህል ማጀት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ ከሚቀልጥ አለት እስከ ጨው ግግር መልክዓምድር የታደለች ሀገር ስትሆን በቱሪዝም ዘርፉ ይህችን ሀገር ለማስተዋወቅ የበኩላቸውን አሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከጂኦቱሪዝም ባለሙያው አቶ እንቁ ጋር ስለህይወት መንገዳቸው ባደረግነው ቆይታ፤ የተለያዩ ጉዳዮችን ተመልክተናል። በግል ሕይወታቸው ስላሳለፏቸው ውጣ ውረዶች ዳስሰናል፡፡ በጂኦቱሪዝም መስክ እንደ ሀገር ያለንን ፀጋ እና እየተጠቀምንበት ያለውን ሁኔታ ከተጨባጭ ልምድና ተሞክሮ በማስተሳሰር ቃኝተናል፡፡ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ነው ያሉትን ምክረ ሃሳብም እንዲያክሉ አድርገናል፤ መልካም ንባብ!
ለጂኦቱሪዝም ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ አስቀድመን “ጂኦቱሪዝም ማለት ምን ማለት ነው?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች፣ ዋሻዎች፣ የሰሜንና የባሌ ተራራዎች የመሳሰሉት የሥነ ምድር ሀብቶች ናቸው። እነዚህ ሀብቶች ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር በማስተሳሰር ሲገለጡ፤ የሚታየው ሀብት እና ፀጋ የሰውን ልጅ ቀልብ ስቦ በመያዝ በቦታው እንዲቆይ የሚያደርግ ነው። ጠቅለል ሲደረግ ጂኦቱሪዝም ማለት የሥነ ምድር ጉብኝት ሲሆን፤ ከመሬት እና ከአለት ጋር የተገናኘ ነው፡፡
ጂኦቱሪዝም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለምም አዲስ የመጣ የቱሪዝም አቅጣጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ ሁሉም ዓይነት ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መስህቦች አሏት፡፡ ዓለም ላይ ካሉ የቱሪዝም መስህቦች ውስጥ ኢትዮጵያ የሌላት የበረዶ ላይ ሸርተቴ ብቻ ነው፡፡ የቱሪዝም ሀብቱን መልክ ለማስያዝ በተለይም ጂኦቱሪዝም (የሥነ ምህዳር የጉብኝት ቦታዎች) ከዛሬ ሦስት እና አራት ዓመታት በፊት በባህልና ቱሪዝም ተጠንቶ በፖሊሲ ደረጃ ተቀርጾ እንዲገባ መደረጉን የገለጹት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ከየትኛውም የቱሪዝም ሀብቷ በይበልጥ ያላት ጂኦቱሪዝም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
“የጂኦቱሪዝም ሀብትን ለረጅም ጊዜ ሳንጠቀምበት ቆይተናል፤ አሁንም በሚፈለገው ልክ እየተጠቀምንበት አይደለም” ያሉት ባለሙያው፣ እንዴት ወደ ዘርፉ እንደተሳቡ ሲያብራሩ፤ “አያቶቼን ለመጠየቅ ወደ ገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ስሄድ፤ አፈሩ ተሸርሽሮ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው አለቶችን እመለከት ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- በአባይ ሸለቆ ውስጥ ጂፕሰም፣ ሳንድስቶን፣ ላይምስቶን የመሳሰሉ አለቶች ይገኙበታል፡፡ ይህንን ድንቅ ተፈጥሮ ወደ አካባቢው ስጓዝ እመለከተው ስለነበር በልጅነት አዕምሮዬ ተቀርጾ ቀርቷል፡፡ በኋላም በቤተሰቦቼ የስራ ዝውውር አማካኝነት ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ደብረ ማርቆስ መሄዴ ከተፈጥሮ ጋር የበለጠ እንድተዋወቅ መሰረት ጥሎልኛል፡፡ ወንዞችን፣ ተራሮችን፣ የተለያዩ የአፈር አይነቶችን እያየሁ ማደጌ ለተፈጥሮ ልዩ ፍቅር እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ ይህም ነው አሁን የጂኦቱሪዝም ባለሙያ ለመሆን መነሻ ምክንያት የሆነኝ” ብለዋል፡፡ ይህንን በልጅነት አዕምሮ የተቀረጸ ጥልቅ የተፈጥሮ ቁርኝት ይዘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ በመግባት ጓደኞቻቸው ህክምናና ኢንጂነሪንግ ሲመርጡ እሳቸው ግን በወቅቱ ምርጫቸውን የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል አደረጉ፡፡
በ1985 ዓ.ም፣ በዩኒቨርስቲው የ4ኛ ዓመት ተማሪ በነበሩበት ወቅት በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት እና ግጭት ለ3 ወራት ታስረዋል፤ ለአንድ ዓመት ደግሞ እንዳይማሩ ታግደዋል፡፡ በዚህ መሀል ነበር ውስጣቸው የነበረውን አስጎብኚነት መሰልጠን የጀመሩት፡፡ የዩኒቨርስቲው እገዳም ተነስቶ የጀመሩትን ትምህርት ቢቀጥሉም ለምርቃት የበቁት ሁለቱንም በማጠናቀቅ ነበር፡፡ የሁለት ሙያ ባለቤትም መሆን ቻሉ፡፡ ከተመረቁ በኋላ ሚድሮክን ጨምሮ የተለያዩ የሀገር ውስጥ እንደ ወለጋ፣ ሻኪሶና ሀገረማሪያም እንዲሁም የውጭ የማዕድን ኩባንያዎች ውስጥ ለ10 ዓመታት ያህል ሰርተዋል፡፡
በሂደት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት የማዕድን ኩባንያዎች ተዘጉ፡፡ በዚህን ጊዜ ወደ ቱሪዝሙ ሥራ በሙሉ ጊዜያቸው ገቡ፡፡ ቱሪዝም ውስጥ እያሉ ፍቅሩ ስላለቀቃቸው ወደ ማዕድን ስራው ተመልሰው ገቡ፡፡ የማዕድን ዘርፉም በተጨባጭ ሀገርን መለወጥ የሚችል መሆኑን በተግባር ተገነዘቡ። በወቅቱ ማለትም በ1980ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የወርቅ ምርት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ሀብት ገቢ መጠንን በከፍተኛ ድርሻ ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ይህ ለእሳቸው ጥሩ ዕድልን ፈጠረላቸው፡፡ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ተግባር መከወን፤ በሥራቸውም ተመጣጣኝ ገቢ ማግኘት ቻሉ፡፡ ይህም ለሥራው የበለጠ ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረጉን አቶ እንቁ ያስታውሳሉ፡፡
ወደ ቱሪዝም ዘርፉ ሲገቡም በማዕድን ምርምር በተለይም ወርቅ ፍለጋ ላይ በተሰማሩበት ወቅት ተራሮች፣ ስምጥ ሸለቆዎች የተሰሩበት ዋና መሰረት የእሳተጎሞራ ፍንዳታ መሆኑን እንደተረዱ ይናገራሉ፡፡ “በማዕድን ምርምር ሙያ ዘርፍ ያለው ሣይንሳዊ ትንታኔ እንደሚያስረዳው፤ እሳተጎሞራ ከመሬት ውስጠኛ ክፍል የወርቅ ማዕድንን ይዞ የመውጣት አቅም እንዳለው ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ እሳተጎሞራን በቱሪዝሙ ዘርፍ ለማስተዋወቅ ጉጉት አደረባቸው፡፡ ጂኦሎጂና ቱሪዝም ግንኙነታቸው የተሳሰረ ሆኖ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ የስምጥ ሸለቆዋ ንግስት በሆነችው አፋር ክልል ነው ብለዋል፡፡
“በጂኦቱሪዝሙ መስክ ኢትዮጵያ ሳትታወቅ ቆይታለች፡፡” የሚሉት ባለሙያው “ዓለማችን ላይ ከሚገኙ 5 ታላላቅ የእሳተጎሞራ ውጤቶች በተለይም ንቁ የእሳተጎሞራ ስፍራዎች መካከል ኤርታሌ አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን በዘርፉ የሚገባውን ያህል አልተጠቀምንበትም” የሚሉት አቶ እንቁ፣ ለ20 ዓመታት ጥናትና ምርምር በማድረግ እንዲሁም በማስጎብኘት የጂኦቱሪዝም ዘርፍ በተለይም አፋር ላይ ያለውን ኤርታሌንና ዳሎልን ለዓለም ለማስተዋወቅ ብርቱ ጥረት ማድረግን ተያያዙት፡፡ አሁንም ጥረታቸውን አጠናክረው በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በጂኦቱሪዝም ዘርፍ ምን ያህል ተጠቅማለች? ምንስ ይቀራታል? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ “ኢትዮጵያ ያላት ሀብት እና እየተጠቀመች ያለው አይጣጣምም፡፡ የተፈጥሮ ሀብቱ አለ፤ ነገር ግን ያለውን ያህል ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ በእምነት ተቋማት እንዲሁም በሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ውስጥ ያሉ የእውቀት ማዕከል የሆኑ ቅርሶች፣ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት እና የታሪክ ድርሳናትን ወደ ቱሪዝም ሀብትነት ቀይሮ የማስጎብኘቱ ስራ በሚገባው ልክ አልተሰራም፡፡ የጂኦቱሪዝም ሀብቶቻችን እንደ ሀገር ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች፣ አቀማመጣቸውና የተፈጥሮ ፀጋቸው ልዩ የሆኑ ተራሮችና ሸለቆዎች ብዙ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡትን የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች እንኳን ብንመለከት ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህ ሀብቶቻችን ከእኛም አልፈው የዓለም ሀብቶች ሆነዋል፡፡
ተጠንተው በጽሑፍ ያልቀረቡም ቅርሶች አሉን፡፡ ለምሳሌ በሀገሪቱ በብዛት አስደናቂ ፏፏቴዎች አሉ፤ ነገር ግን ሥነ ምህዳሩን ከማሳመር እና ከመጠበቅ ባሻገር ለዘርፉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። አሁን ላይ ጅማሮዎች ቢኖሩም ከዚህ በበለጠ ትኩረት መስጠት ያስፈልገዋል፡፡
አፋር ክልል ውስጥ የሚገኘው በእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ የተፈጠረው የሥነ ምህዳር መልክ በዓለም ከአምስቶቹ አንዱ ነው፡፡ ጨውና እሳት አንድ ላይ ያሉበት በዓለም ብቸኛው ስፍራም ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት ሲፍለቀለቅ የቆየና ከዓለም የተለየ የተፈጥሮ ፀጋ በቦታው ቢኖርም ከተለያዩ ሀገራት ብዙ ሺህ ዶላር ከፍለው ለማየት የሚመጡትን ጎብኚዎች ለማስተናገድ በቂ የሆነ መጸዳጃ ቤት፣ የቀዘቀዘ ውሀ፣ መታጠቢያ የለውም፤ የተመቻቸ መሰረተ ልማትም እንዲሁ” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
“የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አስጎብኚው የማያውቀው ነገር ያለ አይመስለውም፡፡ ይሁን እንጂ የጂኦሎጂ እውቀት ያለው የቱሪዝም ባለሙያ በጣም ጥቂት ከመሆኑ አንጻር ባለሙያዎችን ማሰልጠን ግዴታ ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ በዘርፉ ሙያተኞችን ለማፍራት የጂኦቱሪዝም ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ አያይዘው ገልጸውልናል። ስለ አፋር እና ስምጥ ሸለቆ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጉብኝት ፕሮግራሞች እንዲመሩ የማብቃት ስራ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ በዚህም በጂኦቱሪዝሙ ላይ እየደወሉ ይጠይቁ የነበሩ ባለሙያዎች አሁን ላይ ራሳቸውን ችለው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ባለሙያው አክለዋል፡፡
“የቱሪዝም ባለሙያ መሆን ሀገሪቱን በተጨባጭ ለማወቅ እድል ይፈጥራል። ለ30 ዓመታት ያህልም በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሬያለሁ፡፡ የሚያስደንቀው የህዝቦችን አንድነትና መመሳሰል ለማየት ችያለሁ፡፡” ሲሉም ዘለግ ያለ ልምድ እንዳላቸው አካፍለውናል፡፡
“የጂኦቱሪዝም ፍቅር ለሌሎችም ይጋባል” ሲሉ የገለጹት ባለሙያው፤ ዛሬ ላይ ልጃቸውም ፈለጋቸውን ተከትላ በዘርፉ ተሰማርታ ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳን ልጃቸው በማኑፋክቸሪንግ ኢንጂኒየሪንግ የተማረች ቢሆንም በቱሪዝም ፍቅር መጠለፏን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ልምዳቸውና ተሞክሯቸው በመነሳት መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን እንዴት ይመለከቱታል? የሚለው የዝግጅት ክፍላችን ጥያቄ ነበር፡፡ አቶ እንቁ ሲመልሱም፣ “መንግስት እንደ ሀገር ወሳኝ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉን አንዱ በማድረግ ለማሻሻል እና በውጤታማነት ለመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን እየከወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ደረጃ ለዘርፉ ትኩረት የተሰጠው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ይህም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መነቃቃትና ማደግ ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገር አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማትና አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመገንባት አንጻር የተሰራው ስራ አመርቂ ነው፡፡ እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ ላይ የተሰራው ስራ አስደማሚ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን በማበረታታትና በማነቃቃት ረገድ ድርሻው የጎላ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንቅስቃሴ ማድረጉ ወደፊት ቱሪዝም ልክ እንደ ቡና፣ ቆዳና ሌጦ፣ ቅመማቅመም እና ወርቅ የመሳሰሉት ሀብቶች የኢኮኖሚ ምንጭና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ቱሪስት የሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች ለምሳሌ እንደ አፋር… ያሉ አካባቢዎች ላይ የተሰጠው ትኩረት ያለውን የቱሪዝም ሀብት ያህል ነው ለማለት አያስደፍርም” ብለዋል፡፡
ቱሪዝሙ በሚፈለገው መጠን ወሳኝ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን መንግስት የጀመረውን መነቃቃት ማስቀጠልና ሀገራዊ ሰላም ላይ መስራት ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት የሆነውን ማህበረሰብ ስለቱሪዝም ጽንሰ ሀሳብ ግንዛቤ መፍጠርና ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊና ማደግ መስህቦቹን “ሀብቶቼ ናቸው” ብሎ እንዲጠብቃቸውና ለቱሪስቶችም መልካም አቀባበል እንዲያደርግ እገዛ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል፡፡
በለይላ መሀመድ