የቱሪዝም መዳረሻነት ጉዞ

አዲስ አበባ “ከተማ” የሚለውን የወል ስም ከሚጋሩ በርካታ ከተሞች የሚለያት የራሷ ፀጋ አላት፡፡ ከተማዋ ከተማ ብቻ አይደለችም፡፡ ከአገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘረጋ ኃላፊነትን በብቃት እየተወጣች ዘመናት የተሻገረች ከተማ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ በሁሉም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሕብረት እና በአንድነት መኖራቸው “ትንሿ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ያሰጣት የጋራ ቤት፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እንዲሁም የትምህርት እና የምርምር ማዕከል፣ የብዝሃ ሕይወት ሃብት ጎተራ፣ የሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ቅርስ ማጀት ነች፤ አዲስ አበባ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማት ከተማነታቸው ከሚጠቀሱ በጣት የሚቆጠሩ ከተሞች አንዷ የሆነችው አዲስ አበባ፤ በዘርፉ የሚቀድሟት የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ እና የሲውዘርላንዷ ጀኔቫ ከተሞች ብቻ ናቸው። መዲናዋ የበርካታ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ነች፡፡ለአብነት ያክል፡- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም የበርካታ ሀገራት ኢንባሲዎች ከትመውባታል፡፡

ከላይ በጥቂቱ ለመግለፅ የተሞከረው የአዲስ አበባ ሁኔታ ከከተማዋ አልፎ ለአገር የሚበጅ ትልቅ ሃብት እንዳላት የሚጠቁም ነው። በዚህ ጽሑፍ ከአዲስ አበባ እልፍ ፀጋዎች ውስጥ ከከተማ ቱሪዝም ጋር የተያያዘውን አንድ ዘለላ በመምዘዝ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ ከተማዋ ከቱሪዝም አንፃር ያላትን ሃብት፣ ሃብቱን አልምቶ ለመጠቀም የሄደችበት ርቀት፣ ያሉባትን ጉድለቶች እና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ የሚመለከታቸውን አካላት ሀሳብና አስተያየት በጽሑፉ አካትተናል፡፡

የአዲስ አበባ የቱሪዝም አቅም

የከተማዋ የቱሪዝም ሀብት ጭምር የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአፍሪካ ወጣቶች በተጐበኘበት ወቅት

አዲስ አበባ፤ ለከተማ የቱሪዝም መስዕብነት ተመራጭ ሊያደርጓት የሚችሉ አቅሞችን በእቅፏ የያዘች ስለመሆኗ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ በመጣው የማይስ (MICE) ቱሪዝም አዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርጓትን ዕድሎች መያዟን በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2022 በወቅቱ የኢትዮጵያ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተብሎ በሚጠራው ተቋም ትኩረቱን በኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ ያደረገው ሰነድ ያመለክታል፡፡ በሰነዱ ከተጠቀሱት መሰረታዊ  ነጥቦች  መካከል፡- አዲስ አበባ የምትገኝበት መልክዓ ምድራዊ ቦታ ስትራቴጂካዊነቷ (Strategic Location and Connectivity)፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነቷ (Institutional and Diplomatic Hub)፣ ለትላልቅ ጉባኤዎች መከወኛ የተደራጁ ቦታዎች መያዟ (Conference Facilities and Venues)፣ የባህል እና የቱሪስት መስህቦችን መታደሏ (Cultural and Tourist Attractions)፣ የኢኮኖሚ እና የዕድገት ተነሳሽነቷ (Economic and Developmental Initiatives) እንዲሁም አበረታች የመንግስት ድጋፍ እና ፖሊሲ (Government Support and Policy) ለከተማ ቱሪዝም መስፋፋት እና ማደግ በወሳኝነት ተጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ብዝሐነትን በውብ ጥበብ ሸምና፣ በረቀቀ ቅኔ ሰምና ወርቁን አዋህዳ፣ በከፍታ ላይ ከፍ ብላ፣ በጊዜ ዑደት ውስጥ እንደ ዕንቁ ደምቃ እየታየች ያለችው አዲስ አበባ፤ ለቱሪዝም ዕድገት እና ተጠቃሚነት የሚያግዙ እርሾዎች እንዳሏት የከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር  ይመሰክራሉ። እንደሳቸው ገለፃ፤ አዲስ አበባ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ኢንባሲዎች እና ቆንስላዎች መቀመጫነት መመረጧ፣ ኩራታችን በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ብዙ ዓለም አቀፍ ተጓዦች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበት እና በውስጧ የሚያልፉበት ዕድል መፈጠሩ፣ 1 ሺህ 500 ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ ማዕከል እና 657 ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያለው የአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ የጉባኤ ማዕካላት ያላቸው ከ100 በላይ ባለኮከብ ሆቴሎች በመዲናዋ መገኘታቸው ለዘርፉ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ የማይስ ቱሪዝም ሁነቶችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማስተናገድ የሚችል በሙያ፣ በዕውቀትና በልምድ የካበቱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው መሥራታቸው በአዎንታነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው፡፡

በአዲስ አበባ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና መሰል የአደባባይ ሁነቶች መከናወናቸው፣ የተለያዩ ሙዚየሞች (የአዲስ አበባ ሙዚየም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ኢትኖግራፊክ ሙዚየም…) መኖራቸው፣ ታሪክን የሚነግሩ ሐውልቶች መገኘታቸው፣ ብዝሃ-ሕይወትንና ቅርስን አዋህደው የያዙ ፓርኮች (አንድነት፣ እንጦጦ ፓርክ…) ለአገልግሎት መብቃታቸው ለመዲናዋ ቱሪዝም እንደ ትልቅ ገጸ-በረከት የሚወሰዱ መሆናቸውን የጠቆሙት ደግሞ የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያ፣ ተመራማሪ፣ ጸሐፊና መምህር አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ናቸው።መምህር አያሌው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ በአዲስ አበባ ሙዚየሞች፣ በሕንፃቸው እና በውስጣቸው በያዟቸው ዘመን ተሻጋሪ  ቅርሶች ለጎብኚዎች ተመራጭ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች የዕምነት ተቋማት መገኘታቸው፣ የተለያየ ዘመን ተገንብተው አገልግሎት የሰጡ እና እየሰጡ ያሉ አብያተ መንግስታት መኖራቸው፣ እንደ ፍልውሃ ዓይነት ተፈጥሯዊ ፀጋን መታደሏ፣ የትልቁንና ትንሹን የአቃቂ ወንዝ ጨምሮ በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉ ወንዞች የሚፈሱባት መሆኗ … ከሌሎች መሰል ከተሞች የተለየች እንድትሆን ያግዛታል፡፡

የቱሪዝም አቅምን ወደ ውጤት ቀያሪ ጅምሮች

የእንጦጦ ፓርክ ከፊል ገፅታ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም መዳረሻነት ተመራጭ የሆኑ ከተሞች ደረጃ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያሳየችው እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚበረታታ ነው፡፡ መዲናዋን ሥምና ግብሯን በሚመጥን ደረጃ ላይ ለማድረስ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል። በሂደት ላይ ያሉም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻነት ከፍ ከማድረግ፣ ለተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና ስብሰባዎች የሚመጡ እንግዶች የምትመች፣ ቆይታቸውን የሚያራዝሙባት እንድትሆን እና በዘርፉ ተወዳዳሪነቷን ከማሳደግ አንፃር ያላቸው ፋይዳ ትልቅ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

አቶ አቤል መኮነን የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት ባለሙያዎች ማህበር ጸሐፊ ናቸው፡፡ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ በባለሙያነት እና በአመራርነት ለ10 ዓመታት ያህል ያገለገሉ ሲሆን፤ ለዘርፉ ቅርበት እንዳለው ሠው ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለቱሪዝሙ መስክ ያላቸውን ፋይዳ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ በከተማዋ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎች ተሠርተው ለአገልግሎት በቅተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የእንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሁም በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የለሙት የመንገድ መሰረተ ልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ልማቶች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማደግ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅት ባለሙያዎች ማህበር ጸሀፊው አክለውም፤ የከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻነት እንዲያድግ መንግስት ምን ያክል በትኩረት እየሠራ እና ሥራውም ውጤት እያመጣ እንደሆነ የእንጦጦ ፓርክን በማሳያነት በመጥቀስ የሚከተለውን ሃሳብ አጋርተዋል፤ “አዲስ አበባን ከላይ ወደታች ለመመልከት ምቹ መደላድልን አስገኝቷል፡፡ ከፓርኩ በተጨማሪ ጥንታዊውን ቤተ መንግስትና የእንጦጦ ማርያም ሙዚየም ለማስተዋወቅ እና ለማስጎብኘት እድል ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለመዝናኛነትና ለማረፊያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ዘመናዊ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ በኮሪደር ልማቱ የለሙት የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጽዱና ምቹ ሆነው መሠራታቸው ቱሪስቶች ቀኑን ሙሉ የተለያዩ መዳረሻዎችን ሲጎበኙ ከዋሉ በኋላ ወደማረፊያ ክፍሎቻቸው ከመግባታቸው በፊት የእግር እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የአዲስ አበባ ሁኔታ ደግሞ ለዚህ ምቹ አልነበረም፡፡ አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የመጣው ውጤት የሚያስደንቅ ነው፡፡ በልማቱ የተካተቱ መንገዶች ዳርና ዳር  ጽዱ፣ አረንጓዴ እና ምቹ በመሆናቸው፤ ደህንነቱ ለተጠበቀ እንቅስቃሴ እና አረፍ ብሎ ለመዝናናት ተጨማሪ አቅም የፈጠሩ ናቸው። በገበታ ለሃገር መርሃ ግብር ተይዘው የተገነቡ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ለመዲናዋ ሌላ አማራጭ መሆን ችለዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ሃሳብ የሚስማሙት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር  በበኩላቸው፤ በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያላት ዕምቅ የቱሪዝም ፀጋ ከመግለጥ በተጓዳኝ ለከተማዋ አዲስ ገፅታ እና ውበት መስጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም በሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች (ቱሪስቶች) ከተማዋን በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ወደሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ወይም ወደ ሌሎች የዓለም አገራት ለሚደረጉ ጉብኝቶች እንደ መሸጋገሪያ ድልድይነት ይጠቀሙባት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ያ ሁኔታ እየተለወጠ መምጣቱን እና አዲስ አበባ ራሷን ወደ ቻለች የቱሪስት መዳረሻነት እየተቀየረች መምጣቷን አብራርተዋል፡፡

ከተማዋን ሁነኛ የቱሪዝም ማእከል ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ያክል ወሳኝ መሆናቸውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን በማሳያነት የጠቀሱት አቶ ሃፍታይ፤ “መታሰቢያው የአፍሪካውያን እና የዓለም ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ድል ማሳያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ጦርነት ተጋድሎ ከማሳየት በተጨማሪ፤ የተለያዩ ዓይነት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ ኤግዚብሽኖችን፣ ስፖርታዊ ውድድሮችን፣ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችንና መሰል ሁነቶችን ለማሰናዳት እና ለማስተናገድ ምቹ፣ ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ አዳራሾችን ይዟል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሽከርካሪ ማቆሚያ አለው፡፡ የምግብ፣ መጠጥ እና መሰል አገልግሎት መስጫዎች አሉት፡፡ ስብሰባ ላይ የሚደረጉ ምክክርና ውይይቶችን በተለያየ ቋንቋ ለታዳሚው ለማሰራጨት፣ የሚዲያ የቀጥታ ስርጭት ለመስጠት … የሚያግዙ እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተገጥመውለታል፡፡ ይህ ደግሞ የጎብኚዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያግዝ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለው እንዳብራሩት፤ የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባን ውበት በማጉላት፣ ገፅታዋን በማሻሻል፣ ለነዋሪዎቿና ለእንግዶቿ በማመቻቸት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ መሰል ከተሞች ጋር ተወዳዳሪነቷን በመጨመር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ ነው።ከዚህ ቀደም ከተማዋ የምትወቀስበትን የውበትና ፅዳት ጉድለት ምላሽ እየሰጠ ያለው የኮሪደር ልማቱ፤ ዓለም አቀፍ እንግዶች ቀን ቆርጠው የመጡለትን ስብሰባ፣ ኮንፈረንስ እና መሰል ሁነት ባጠናቀቁ ማግስት ወደመጡበት ከመመለስ ይልቅ በመዲናዋ የሚያደርጉትን ቆይታ እንዲያራዝሙ ያደርጋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ የመዲናዋን ገፅታ በመሰረታዊነት የለወጠ እና ዘመናዊነቱን ከፍ ያደረገ መሆኑ፤ በቱሪዝም ዘርፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ ማህበራት ወዘተ ራሳቸውን ከከተማዋ ወቅታዊ ለውጥ ጋር የተዛመደ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በአሁኑ ወቅትም ይህ ሁኔታ በሆቴሎች፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች እየታየ ነው፡፡

የቦሌ ኮሪደር ልማት ከፊል ገፅታ

የአዲስ አበባ ከተማ ያላትን ዕምቅ የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ከሠራቻቸው ጅምር ሥራዎች በተጨማሪ ትኩረት ማድረግ ያለባት ጉዳዮች እንዳሉ ያነጋገርናቸው ሠዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የሠላምና ፀጥታ ጉዳይን በተመለከተ ራሱን የቻለ የቱሪስት ፖሊስ መዋቅር መፍጠርና ወደ ሥራ ማስገባት እንዲሁም የከተማዋን ዕምቅ የቱሪዝም ሃብት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ማስተዋወቅ ላይ መተኮር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በጉድለት የተነሱ አስተያየቶች ትክክለኛ ስለመሆናቸው ያመኑት አቶ ሃፍታይ በበኩላቸው፤ የመዲናዋን የቱሪዝም ፀጋ በተለይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቁ እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራው ዋና ችግር ከበጀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህም ተደራሽነታቸው ሰፊ በሆኑ እንደ ሲኤንኤን (CNN) ባሉ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ለማስተዋወቅ የተያዘው ዕቅድና ጥረት አለመሳካቱን አንስተዋል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ በመስጠት መዲናዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በ2017 በጀት ዓመት በትኩረት ለመሥራት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የሚያገኙትን ዓለም አቀፍ መድረኮች እና ዕድሎች በመጠቀም የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የአዲስ አበባን የቱሪዝም አቅም በማሳደግ ቀላል የማይባል ሚና እየተጫወቱ መገኘታቸው በበጎ ጎኑ የሚነሳ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ላይ በስፋት የሚሠራበትን የቱሪስት ፖሊስ ጉዳይ በከተማዋ ተግባራዊ ለማድረግም ጅምር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ከፍተኛ የቱሪዝም ፀጋ እና ዕድል ያላት መሆኑ መሬት በነካ ውጤት መገለጥ አለበት፡፡ ፀጋ እና ዕድሉ ሃብት ማፍራት ይኖርበታል፡፡ ሃብቱ በነዋሪዎቿ እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይገባዋል፡፡ ይህ ውጤት እንዲመጣ የተጀመረውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ህብረተሰቡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና የእንግዳ ተቀባይነት እሴትን በተግባር በሚገልጥ መልኩ ተቀብሎ የማስተናገድ ልምዱን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል፡፡

መንግስት የ10 ዓመቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚለው ማእቀፍ ውስጥ ካካተተው ውስጥ አንደኛው ቱሪዝም ነው፡፡ 59 የሚሆኑ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል አዲስ አበባን ጨምሮ እንደ ሀገር መገንባት በሚል አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ ነው፡፡ አሁን እየታዩ ያሉት የቱሪዝም መዳረሻዎችም የዛ ውጤቶች ናቸው፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review