የትግራይ ክልልን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት የሚጥሩ ጥቂት የቀድሞ የህወሃት አመራር አባላትን ህዝቡ በጋራ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ

AMN ግንቦት 16/2017

የትግራይ ክልልን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት የሚጥሩ ጥቂት የቀድሞ የህወሃት አመራር አባላትን ሕዝቡ በጋራ በቃችሁ ሊላቸው እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አቶ ጌታቸው ረዳ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ትግራይን የጦርነት አውድማ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው አካላትን ምኞት ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በህገ-መንግስቱና በፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈናቃዮችን በሚፈለገው ልክ ወደ ቀያቸው መመለስ ያለመቻሉን አንስተዋል።

ለዚህም በትግራይ ክልል በስልጣን ላይ ያለው ሀይል የህዝቡን አጀንዳ ከማስቀደም ይልቅ ስልጣንና ስልጣን ብቻ በማለቱና እዚህ ግባ የሚባል ስራ ባለመስራቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል አሁን የተፈጠረው ችግር የትግራይ ፖለቲከኞች የፈጠሩት መሆኑን በመግለጽ፤ አመራሩ የያዘው ግትር አቋም ትግራይ ከአደጋ ስጋት እንዳትወጣ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የህዝብን ጥቅም ከግምት ውስጥ ሳማያስገባ ፍላጎቱን በሀይል ለማሳካት እየገለጸ መሆኑንም አስረድተዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዓላማው ችግሮች በህገ-መንግሥታዊ አውድ እንዲፈቱ ማድረግ ቢሆንም፤ ከስህተታቸው የማይማሩት ጥቂት የቀድሞ የሕወሃት ሀይሎች ለስልጣን ሲሉ ወደ ግጭት ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአሁን ቀደሞ የተፈጠረው ግጭት የትግራይን ህዝብ ዋጋ እንዳስከፈለው የገለጹት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ የትግራይ ህዝብ ተመሳሳይ ነገር እንዳይገጥመው የእነዚህን ሀይሎች እኩይ ፍላጎት እንዲያውቅ እያጋለጥን ነው ብለዋል።

በስልጣን መቀጠል የሚፈልጉ ጥቂት የአመራር ቡድኖች ልጆቻቸውን አስቀምጠው የደሀ ልጆችን ለእሳት እንደማገዱ በተግባር ያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሄ ሀይል የእኔ ስልጣን ካልተረጋገጠ ሁሉም ነገር ገደል ይግባ የሚል መሆኑን ገልጸው፣ ዓላማውም ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን አንስተዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ዳግም የትግራይ ህዝብ ወደ ግጭት ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት ማጋለጥ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ግንኙነት ከፌዴራል መንግስት ጋር መሆኑ ግድ ነው ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ ከእከሌ ጋር ሆኜ ማጥቃት እችላለሁ የሚለውን ማጋለጥ አለብን ብለዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በትክክል ገቢራዊ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው፣ የትግራይ ህዝብ ለተወሰኑ ሰዎች የስልጣን ጥም መሞት የለበትም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት 99 በመቶ የሚሆነው አመራር ሰላም ፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ እነዚህን ጥቂት የግጭት ጠማቂዎች በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ማለታዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review